Fana: At a Speed of Life!

ለወላጆች የውሳኔ ስልጣን የሰጠው ደንብ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ትምህርት እና ሥልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን የግል ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ የጸደቀው ደንብ ለወላጆች የውሳኔ ስልጣን የሰጠ ነው አለ።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢዘዲን ሙስባህ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የግል ትምህርት ቤቶች የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ እንዲያደርጉ የሚያስችል ደንብ ጸድቋል ብለዋል።

ደንቡ የግል ትምህርት ቤቶች በየጊዜው ያለአግባብ እና ምክንያታዊ ባልሆነ ሁኔታ የሚያደርጉትን ጭማሪ ማስቀረቱን ተናግረዋል።

የግል ትምህርት ቤቶች የሚያደርጉት የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ አስፈላጊነትን የሚያሳይ መነሻ ሀሳብ ማቅረብ እና የውይይት መድረክ ማዘጋጀት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በትምህርት ቤቶቹ ደረጃ እስከ 65 በመቶ ድረስ በተቀመጠው ጣሪያ መሰረት ከወላጆች ጋር በመወያየት አብዛኛው ወላጅ ሲስማማ ጭማሪው ወደ ተግባር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እስካሁን በ1 ሺህ 195 ትምህርት ቤቶች ወላጆች ተገኝተው ትምህርት ቤቱ ባቀረበው የክፍያ ጭማሪ መነሻ ሀሳብ መሰረት መወያየታቸውን ገልጸው፤ 948 ትምህርትቤቶች ከስምምነት ደርሰዋል ብለዋል።

እንዲሁም በወላጆች እና በትምህርት ቤቶቹ መካከል ጭማሪውን አስመልክቶ አለመስማማት ቢፈጠር ባለስልጣኑ ሁለቱንም ሪፖርቶች በመመልከት የራሱን ውሳኔ እንደሚያሳልፍም አብራርተዋል፡፡

ደንቡን ለማውጣት በርካታ ባለድርሻዎችን ያሳተፉ ጥናቶች መደረጋቸውን ገልጸው፤ በዚህ መሰረት ወላጆችን ሳይጎዳ የትምህርት ጥራትን እንዲያረጋግጥ መደረጉን ገልጸዋል።

ደንቡ ወላጆች በተደጋጋሚ ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ የግል ትምህርት ቤቶች ትርፍ ከማግኘት ባሻገር ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነት ስላለባቸው የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ላይ ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አሁን የተደረገው የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ ለቀጣይ ሶስት አመታት እንደሚያገለግልም አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት እና ሥልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢዘዲን ሙስባህ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ተከታዩን ማስፈንጠሪያ በመጫን ይከታተሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.