የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አስደማሚ ለውጥ የታየበት ነው – ራሚዝ አላካባሮቭ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት ረዳት ዋና ጸሃፊ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አላካባሮቭ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አስደማሚ ለውጥ የታየበት ነው አሉ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን ራሚዝ አላካባሮቭ (ዶ/ር) ባሰናበቱበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር ስኬታማ ትብብር አላት ብለዋል።
በኢትዮጵያ እና በተባበሩት መንግስታት መካከል የቆየው መልካም ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ አስደናቂ ለውጦችን ተመልክቻለሁ ያሉት ራሚዝ አላካባሮቭ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ጊዜ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።
በተለይ በከተማ እና በገጠር እየተከናወነ ባለው ሰፊ የለውጥ ሥራ መደነቃቸውን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በከተሞች የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት አማካኝነት አዲስ አበባ እና ሌሎች የክልል ከተሞች እየተቀየሩ መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡
ሌላው አስደማሚ ለውጥ ደግሞ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው በዓለም ትልቁ የሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቢሊየን የሚቆጠር ችግኝ የሚተክል ሀገር አላየሁም በማለት ገልጸው÷ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የልማት ግብን በማሳካት ረገድ ረጅም ርቀት ተጉዛለች ብለዋል።
በቀጣይም በኢትዮጵያ እና በተባበሩት መንግስታት መካከል ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡