በመኸር እርሻ እስካሁን 7 ሚሊየን ሄክታር በዘር ተሸፍኗል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017/18 የመኸር ወቅት እርሻ እስካሁን 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል አሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)።
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ በግብርናው ዘርፍ በመኸር፣ በበልግ እንዲሁም በመስኖ ልማት ሥራዎች ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
በዚህ ዓመት በመላ ሀገሪቱ 21 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመኸር እርሻ በተለያዩ ሰብሎች በዘር እንደሚሸፈን ነው የተናገሩት፡፡
አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የዘር ሥራ የሚከናወንበት በመሆኑ እንደ በቆሎ ያሉ የአገዳ ሰብሎች ቀድሞ መዘራታችን ጠቁመው÷ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስና ሌሎች እንደየ አካባቢው ሥነ ምህዳር እየተዘሩ ነው ብለዋል፡፡
ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እና ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ በመፍጠር ጭምር በመሰራቱ በዚህ ዓመት የተሻለ ምርት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያችሉ የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር እና የተለያዩ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲደርሱ መደረጉን አንስተዋል።
የመኸር የእርሻ ጊዜ ለኢትዮጵያ ትልቁ የምርት ጊዜ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ÷በዓመቱ በአጠቃላይ ከሚመረተው ምርት 70 በመቶ የሚሆነው በዚሁ ወቅት የሚለማ መሆኑን አብራርተዋል።
ዘንድሮ 13 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የሚለማ ሲሆን÷ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት ደግሞ በመካናይዜሽን መታረሱን አመልክተዋል፡፡
በመኸር ወቅት 21 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ከ659 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ መጠቆሙን ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook WMCC
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!