ከንቲባ አዳነች በአዲስ አበባ የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለአሶሳ ከተማ አካፈሉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮሪደር ልማትና ሌሎች ሥራዎች የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለክልል ከተሞች የማካፈል ሥራ እየተከናወነ ነው አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባ አዳነች በዛሬው ዕለት የአሶሳ ከተማን የኮሪደር ልማት ሥራ እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
ከንቲባዋ በጉበኝታቸውም አዲስ አበባ ላይ ባሕል እየሆነ የመጣውን የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ለ40 አቅመ ደካሞች እና የሀገር ባለውለታዎች የሚሆን ባለ አራት ወለል ሕንጻ ግንባታ፣ የምገባ ማዕከል ማቋቋም፣ የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም አካል የሆነው የሕጻናት መጫወቻ ቦታዎች ግንባታን እና የጽዱ ኢትዮጵያ ሥራዎችን በአሶሳ ከተማ አስጀምረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሥራ አቅጣጫ መሰረት የአዲስ አበባን አሮጌ ገጽታ እና የድህነት ታሪክ ለመቀየር በመልሶ ማልማት እና በኮሪደር ልማት ሥራ ከሕዝብ ውይይት እስከ ትግበራ በትኩረት መሰራቱን አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ሕዝቡን የልማቱ ባለቤት በማድረግ የመጣውን ተጨባጭ ውጤት እና ተሞክሮ ማካፈላቸውን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብልጽግና ከዳር እስከ ዳር እስኪዳረስ እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራታችንን እንቀጥላለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡