Fana: At a Speed of Life!

የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የህንድ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ለመሰማራት ያላቸውን ፍላጎት አሳድጓል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ተግባራዊ የተደረጉ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች የህንድ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል አሉ።

አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ተግባራዊ የተደረጉ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች በህንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ናቸው።

የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያው እንዲወሰን እና የውጭ ሀገር ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት መሆን የሚችሉበት አዋጅ መጽደቁ የውጭ ባለኃብቶችን ተሳትፎ የሚያሳድግ ትልቅ ርምጃዎች ናቸው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለኃብቶች ዝግ የነበሩ የኢኮኖሚ መስኮች ክፍት መደረጋቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መሆኑን ነው ያነሱት።

በግብርና፣ በማዕድን፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በባንክና ፋይናንስ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው የህንድ ባለኃብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡

በንግድና በኢንቨስትመንት በኩልም በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ረገድ ላይ እየተሰራ መሆኑን እና የብሪክስ የትብብር ማዕቀፍም ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ በየዘርፉ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ገለጻ እያገኘን ነው ያሉት አምባሳደሩ÷ በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.