Fana: At a Speed of Life!

ተፈጥሮን እንደ ዓይን ብሌን… የሸካቾዎች ሚስጢር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሸካቾ ሕዝቦች ለአያሌ ዘመናት ተፈጥሮን በሚገርም ሁኔታ ሲንከባከቡ ቆይተዋል፤ተፈጥሮን በሚጎዳ ማንኛውም ጉዳይ አይደራደሩም፡፡

ዛፍ መቁረጥ ቀርቶ ያለ ፍቃድ ሐረግ መምዘዝ በሸካቾዎች ዘንድ ነውር እና በጥብቅ የተወገዘ ነው።

በሸካቾዎች ደን ማለት ልክ እንደ በኩር ልጅ ይወሰዳል፤ በዚህም ምክንያት ነው ሁሉ ነገራችን ነው የሚሉትን ደን ልክ እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚጠብቁት።

ሸካቾዎች ተፈጥሮና ደንን የሚጠብቁበት ባህላዊ ሕግና ሥርዓቶችም አሏቸው፤ በሸካቾዎች ባህል ውስጥ የሚከወኑ ሥርዓቶች ሁሉ የአካባቢውን ደን ለመጠበቅ ትኩረት የሰጡ ናቸው።

ሸካቾዎች ተፈጥሮን ጠብቀው ካቆዩባቸው ባህላዊ ሥርዓቶች አንዱ “የኮቦ” ሥርዓት ይሰኛል። ኮቦ ከመኖሪያ ቤታቸው ራቅ ያሉ ሰፋፊ ደኖችን በስምምነት ተከፋፍለው የሚጠብቁበት ሥርዓት ነው።

በኮቦ ባህላዊ የደን አጠባበቅ ሥርዓት የተወሰነ የደን ክፍል የያዘው ግለሰብ በያዘው ደን ውስጥ ማር፣ ቡናና ቅመማ ቅመም እያመረተ መጠቀም ይችላል።

ነገር ግን ይህንን በሚያደርግበት ጊዜ በባህላዊ አስተዳደር የተቀመጡ የጥበቃ ሥርዓቶችን የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት። በዚህም ደኑን እያስተዳደረ የመጠቀም ሃላፊነት ያለበት ግለሰብ በደኑ ላይ ጉዳት ቢያደርስ በባህላዊ አስተዳደሩ ቅጣት ይጠብቀዋል።

ሸካቾች ለዘመናት ደንን ጠብቀው ያቆዩበት ሌላው ሚስጥር “የጉዶ” ሥርዓት በመባል የሚታወቅ ሲሆን÷ ይህ ሥርዓት ባህላዊ የእምነትና የአምልኮ ስፍራዎች የሚጠበቁበት ነው።

ባህላዊ የአምልኮ ሥርዓት የሚከወንባቸው ስፍራዎች ዕድሜ በጠገቡ ጥብቅ ደኖች የተከበቡ ቦታዎች ሲሆኑ “ጉዶ” በመባል ይጠራሉ። ታዲያ በዚህ የተከበረ ስፍራ ሐረግ መምዘዝ እንኳ አይፈቀድም።

በሸካቾዎች ዘንድ ጉዶ ደኑን ጠብቆ የማቆየትና ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ እንዲዘንብ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሎ ይታመናል።

በጉዶ አካባቢ ከደኑ በተጨማሪ በደኑ ውስ የሚኖሩ እንስሳትን ማደን የተከለከለ ሲሆን÷ይህም የዱር እንስሳቱ ተጠብቀው እንዲኖሩ አስችሏል፡፡

ተፈጥሮን በመጠበቅ የተካኑት ሸካቾዎች ደንን ጠብቆ በማቆየት የሚያስችሉ በርካታ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ሲተገብሩ የኖሩ ሕዝቦች ናቸው፤ዓለም ከሚያውቃቸው ጥቂት ስፍራዎች አንዱ የሆነውንና በዩኔስኮ የተመዘገበውን የሸካ ደን ባዮስፌር ሪዘርቭንም ለምድራችን አበርክተዋል።

131 ሺህ 639 ሄክታር መሬት የሚሸፍነው የሸካ ባዮስፌር ሪዘርቭ በውስጡ ከ300 በላይ የዕጽዋት ዝርያዎችን፣ ከ200 በላይ አዕዋፋት፣ 50 የአጥቢና 20 የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎችን አቅፎ መያዙን የሸካ ዞን ኮሙኒኬሽን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቢሊየኖች የሚቆጠር ችግኞች በመትከትል ላይ ትገኛለች፤ በመሆኑም የተተከሉ ዛፎች የሀገር እስትንፋስ ይሆኑ ዘንድ መንከባከብና መጠበቅን ከጥበበኞቹ ሸካቾች መማር ይገባል።

በተስፋዬ ምሬሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.