በየካ ክፍለ ከተማ የጎረቤቷን የኤቲኤም ካርድ በመስረቅ ከ580 ሺህ ብር በላይ ወጪ አድርጋ ለግል ጥቅሟ ያዋለችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በየካ ክፍለ ከተማ የጎረቤቷን የኤቲኤም ካርድ በመስረቅ ከ580 ሺህ ብር በላይ ወጪ አድርጋ ለግል ጥቅሟ ያዋለች ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ገለፀ፡፡
የግልተበዳይ ወ/ሮ ሰናይ ቦጋለ እና ወንጀሉን ፈፅማለች የተባለችው ግለሰብ የቅርብ ግንኙነት እና ጉርብትና አላቸው፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የኮተቤ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መርማሪ ረዳት ሳጅን እስጢፋኖስ ገ/ታቲዎስ እንደገለፁት ተጠርጣሪዋ ከግል ተበዳይ ጋር ያላትን ቅርበት ተጠቅማ ወደ ወ/ሮ ሰናይ ቦጋለ መኝታ ክፍል በመግባት ቁም ሳጥን ውስጥ ተቀምጦ የነበረ የዘመን ባንክ ኤቲኤም ካርድን ከእነ ሚስጥር ቁጥሩ ሰርቃ በመውሰድ እና በተለያዩ ጊዜያት ከ580 ሺ ብር በላይ ከባንኩ ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅሟ አውላለች፡፡
የግል ተበዳይ ከሀገር ውጭ የሚኖሩ መሆናቸውን የገለፁት ተወካያቸው አቶ ወርቁ ለገሰ ወይዘሮ ሰናይ ቦጋለ የኤቲኤም ካርዱን ከባንኩ ከወሰዱበት ጊዜ ጀምሮ ተጠቅመውበት እንደማያውቁ እና ባላወቁት ሁኔታ ገንዘቡ ከባንክ ወጪ መደረጉን ባወቁ ጊዜ ለፖሊስ ማመልከታቸውን ተናግረዋል።
ፖሊስ ከባንኩ ባገኘው መረጃ መሰረት በተጠርጣሪዋ ላይ ክትትል በማድረግ በየካ ክፍለ ከተማ ክልል ውስጥ በቁጥጥር ስር እንዳዋላት እና በአሁኑ ወቅትም ምርመራ እየተደረገባት እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ረዳት ሳጅን እስጢፋኖስ ገ/ታቲዎስ የኤቲኤም ካርድ የሚጠቀሙ ግለሰቦች የሚስጥር ቁጥራቸውን ከተቻለ በቃላቸው በመያዝ ወረቀቱን ማስወገድ ይህ ካልተቻለም ሚስጥራዊ ቦታ በማስቀመጥ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡