Fana: At a Speed of Life!

ዘመኑን የዋጀ ቀልጣፋ የኢሚግሬሽን አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ዘመኑን የዋጀ ቀልጣፋ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ፡፡

የአገልግሎቱ የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሃሰን እና የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል፡፡

ወ/ሮ ሰላማዊት በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ÷ ከለውጡ በፊት ዜጎች ወጥነት በሌለውና ተገማች ባልሆነ አገልግሎት ለተለያዩ እንግልቶች ሲዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም የሕግ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በዚህም ዘመኑን የዋጀ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ 11 የሪፎርም አጀንዳዎች ተቀርጸው ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል፡፡

ከ25 ዓመታት በላይ የቆየውንና ኋላቀር የነበረውን የባዮሜትሪክ መረጃ መቀበያ ሥርዓት ወደ ዘመናዊ ሥርዓት በመቀየት አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

ፓስፖርትን ጨምሮ ከ10 በላይ የጉዞ ሰነዶች እንዲዘምኑ መደረጉን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ÷ በዚህም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሲነሱ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን መፍታት መቻሉን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ አቪዬሽን ድርጅት ቁልፍ የሕዝብ መረጃ ልውውጥ ሥርዓት (ፒኬዲ) አባል ማድረግ መቻሉን ጠቁመው÷ ይህም የሀገርን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ከተለያዩ አገልግሎቶች 34 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ÷ በቀጣይ የተገልጋዩን እርካታ የዕለት ተዕለት መለኪያ በማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.