Fana: At a Speed of Life!

ሚድሮክ ከ170 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኩላሊት ሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከ170 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኩላሊት ሕክምና ቁሳቁስ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት ፥ ሚድሮክ 20 የኩላሊት እጥበት ማሽን እና 10 ዘመናዊ አልጋዎችን ድጋፍ አድርጓል፡፡
የተደረገው ድጋፉ 180 ታካሚዎችን ለሶስት ዓመት የኩላሊት እጥበት ሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ከፍለው መገልገል ለማይችሉ 144 ታማሚዎች በዘውዲቱ እና በምኒልክ ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታሎች በየዓመቱ እስከ 25 ሚሊየን ብር በመመደብ ነጻ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ከ5 ዓመት በፊት መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
የዛሬው ድጋፍም የተጀመረውን ነጻ አገልግሎት በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችልና ለታካሚዎች ትልቅ እፎይታ እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል፡፡
የሕይወት አድን ሥራ በፈጣሪም ሆነ በሰው ዘንድ ትልቅ ዋጋ አለው ያሉት ከንቲባዋ ፥ ሚድሮክ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.