Fana: At a Speed of Life!

ለ22 ዓመታት ደም የለገሰው የበጎ ፍቃደኞች አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጅማ ከተማ ነዋሪው አቶ ቃዲ አደም ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 22 አመታት ያለማቋረጥ በአመት ለአራት ጊዜ ደም በመለገስ በርካቶች በደም እጦት ምክንያት ለህልፈት እንዳይዳረጉ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከስጦታዎች የላቀውን የደም ልገሳ በጎ ተግባር የጀመረው የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚከተትልበትና በቀይ መስቀል ክበብ ታቅፎ በበጎ ፍቃደኝነት በሚያገለግልበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳል።

አቶ ቃዲ አደም ለዚህ በጎ ተግባር መነሻ የሆነው አጋጣሚ ደግሞ፥ አንዲት እናት ከብዙ ጥበቃ በኋላ ጸንሳ የወለደችው ጨቅላ ደም አስፈልጎት በወቅቱ የተፈለገው የደም አይነት ባለመገኘቱ ልጇ ለህልፈት በመዳረጉ የደረሰባትን ሀዘን በመስማቱ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

ቃዲ 96 ጊዜ ደም በመለገስ ቀዳሚ በመሆን ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች የአምባሳደርነት እውቅና ተሰጥቶታል።

“ከአቅም በላይ የሆነ ችግር እስካልገጠመኝ ድረስ ደም መለገሴን አላቆመም” የሚለው አቶ ቃዲ፥ በህይወት ዘመኑ 200 ዩኒት ደም የመለገስ ህልም እንዳለውና አሁን ላይ 100 ዩኒት ደም ሊሞላ መቃረቡን ተናግሯል።

ከራሱም አልፎ ቤተሰቦቹን ጨምሮ የቅርብ ጓደኞቹ፣ እንዲሁም የአከባቢው ነዋሪዎች የእሱን አርዓያነት ተከትለው በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሽ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል።

የአቶ ቃዲ አደምን አርዓያነት ከተከተሉ በጎ ፍቃደኞች መካከል የጅማ ከተማ ነዋሪዎቹ እንግዳወርቅ ዘውዱ 56 ጊዜ እንዲሁም ሳልልሽ ከበደ 16 ጊዜ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል።

የጅማ ደም ባንክ የደም ልገሳና አሰባሳብ አገልግሎት የስራ ሂደት መሪ አቶ ሀይደር ሁመር እንደሚሉት፥ ባንኩ ከበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች የሰበሰበውን ደም በጅማና አካባቢዋ የሚገኙ 16 ሆስፒታሎች እንደሚገለገሉበት ተናግረዋል።

በከተማዋ በአሁኑ ወቅት ከ300 ያልበለጡ በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች በቋሚነት ደም እየለገሱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በአካባቢው የደም ፍላጎትን ለማሟላት በአመት 10 ሺህ ዩኒት ደም እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ በተለይም በክረምቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የደም ልገሳው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በወርቃፈራው ያለው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.