Fana: At a Speed of Life!

በሌማት ትሩፋት 9 ነጥብ 4 ቢሊየን እንቁላል ተመረተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብርና ሚኒስቴር በ2017 በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር 9 ነጥብ 4 ቢሊየን እንቁላል ተመርቷል አለ፡፡

የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያስገኘ ነው፡፡

መርሐ ግብሩ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዶሮ ስጋ እና የእንቁላል ምርትን ለማሳደግ በትኩረት መሰራቱን ጠቁመው÷ ለዚህም 150 ሚሊየን ጫጩት ለማሰራጨት ታቅዶ 135 ሚሊየን ጫጩት መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 8 ቢሊየን እንቁላል ለማምረት መታቀዱን ያነሱት ሚኒስትር ዴዔታው÷ አሁን ላይ 9 ነጥብ 4 ቢሊየን እንቁላል ማምረት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል 190 ሺህ ቶን የዶሮ ስጋ መመረቱን ጠቁመው÷ በቀጣይ በመርሐ ግብሩ የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.