Fana: At a Speed of Life!

ተለዋዋጭና ኢተገማች በሆነ ዓለም-ዓቀፋዊ የደኅንነት አውድ ውስጥ ሀገርን ማፅናት ያስቻሉ ስምሪቶች ተካሂደዋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተለዋዋጭና ኢተገማች በሆነ ዓለም-ዓቀፋዊ የደኅንነት አውድ ውስጥ ሀገርን ማፅናት ያስቻሉ ስምሪቶች ተካሂደዋል አለ።

የአገልግሎቱ የ2017 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አቅጣጫ ላይ ግምገማዊ ውይይት ተካሂዷል።

የአገልግሎቱ ስትራቴጂክ አመራሮች በተገኙበት በተካሄደው ውይይት፤ በ2017 በጀት ዓመት ተለዋዋጭና ኢተገማች በሆነ ዓለም-ዓቀፋዊና ቀጣናዊ የደኅንነት አውድ ውስጥ ጫናዎችን በመቋቋም ሀገርን ማፅናት ያስቻሉ ስምሪቶች እና የኦፕሬሽን ሥራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።

በበጀት ዓመቱ ተቋሙ የተሰጠውን መረጃ የመሰብሰብና የመተንተን ተልዕኮ ከመወጣት አንፃር ስትራቴጂክ፣ ኦፕሬሽናልና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን በማመንጨት ለውሳኔ ሰጪ አካላት ግብዓት እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።

የተሰበሰቡ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ ከሌሎች የፀጥታና መረጃ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሕግ የበላይነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን የሚያስችሉ የኦፕሬሽን ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

በተለያዩ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች የተሳተፉና ከብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም በተጻራሪ የተሰለፉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

ይህን ተከትሎም አሁን ላይ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የነበሩ የፀጥታ ችግሮች እየተፈቱ መሠረታዊ መሻሻሎች ታይተዋል፡፡

በሀገሪቱ የተካሄዱ በርካታ ዓለም-አቀፍና አህጉራዊ ጉባኤዎችን እንዲሁም የአቪዬሽን ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ ምንም አይነት ክፍተት እንይፈጠር አገልግሎቱ ውጤታማ ስምሪት ማካሄዱን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫው አመልክቷል፡፡

አገልግሎቱ የሥነ- ልቦና ጦርነትን ለመምራት እና ለማስተባበር በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት መሰረት አድርጎ ከውስጥ እና ከውጭ ሀገራችንን እና የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም ብሔራዊ ደኅንነትን ኢላማ አድርገው የተቃጡ ጦርነቶችን የመመከት፣ የመከላከል እና አስፈላጊ ሲሆንም የማጥቃት እርምጃዎችን በመውሰድ ረገድ ስኬታማ ተግባር ማከናወኑ በመግለጫው ተጠቅሷል።

በበጀት ዓመቱ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ባከናወናቸው ሥራዎች እንደ ተቋም መረጃን የመሰብሰብ፤ የመተንተን እና የመመዘን አቅምን ማሳደግ የተቻለበት፤ ብሔራዊ ጥቅምን ሊያስጠብቁ የሚያስችሉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ስምሪቶች የተከናወኑበት፤ ቴክኖሎጂን መታጠቅ ብቻ ሳይሆን በራስ አቅም ማላመድና ማበልፀግ ላይ ውጤት የተገኘበት እንዲሁም ሀብትን አቀናጅቶ መጠቀም ልምድ የዳበረበት መሆኑ እንደ ጥንካሬ ተነስቷል።

ባለፉት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቷቸው በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች በአሰራር ስርዓት የዘመነ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል የያዘና ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ የታጠቀ እንዲሁም ኢትዮጵያን የሚመስል ተቋም ለመገንባት የተደረገው ጥረት ውጤት የተገኘበት እንደነበር ተገምግሟል።

የመረጃና ደኅንነት ስምሪት ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ተጣጥሞ መካሄድ ስላለበት በቀጣይ የሪፎርም አጀንዳዎችን መከለስና ወቅቱን የሚዋጁ አዳዲስ አቅጣጫዎችን መስቀመጥ እንደሚገባ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

በሚቀጥለው ዓመትም የሀገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ወደ ተሟላ ሰላምና መረጋጋት መለወጥ፤ ለሀገራዊ ምርጫ ምቹ መደላድልን መፍጠር፤ ተለዋዋጭ ለሆኑ ሁኔታዎች ስትራቴጂካዊ ዝግጁነትን ማጠናከር ዋናዎቹ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸው ተነስቷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በቀጣይ ዓመት እንደ ሀገር የሚከወኑ ሁነቶችን ተከትሎ ከውስጥና ከውጭ የሚሰነዘሩ የደኅንነት ስጋቶችን መቀልበስ የሚያስችል የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂና የሎጀስቲክስ ቁመና ላይ እንደሚገኝ በመድረኩ መገምገሙን በመግለጫው አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.