የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የክልሎች የምርት አቅርቦት ትብብርና ትስስር ሊጠናከር ይገባል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የክልሎች የምርት አቅርቦት ትብብርና ትስስር ሊጠናከር ይገባል አሉ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንግስት እና በፓርቲ ትብብር የተከናወኑ አበይት ተግባራትን የሚገመግም መድረክ በድሬዳዋ ተካሂዷል።
አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ትኩረት በሚሹ ጉዳዮችና መሰራት ስላለባቸው ቀጣይ አቅጣጫዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሀገርንና ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው በተለይም የኑሮ ውድነትን በማቃለል ረገድ በቀጣይ ብዙ ስራዎች ይጠበቃሉ ብለዋል።
በዚህ ረገድ ጅምሮቹ ጥሩ መሆናቸውን አንስተው፤ እንደየ ክልሎቹ ነባራዊ ሁኔታ ምርቶችን በመለየትና አቅርቦትና ምርታማነትን በማሳለጥ በቀጣይም ብዙ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በምርት አቅርቦት ረገድ የክልሎች ትብብርና ጥብቅ ትስስር አስፈላጊ በመሆኑ በቀጣይ በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የቅዳሜ እና እሁድ ግብይቶችን ጨምሮ ለገበያ ማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በየደረጃው ያሉ አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።
የኮንትሮባንድ ንግድንና የገበያ አሻጥሮችን በጥብቅ በመከታተል ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት መስራት ይገባልም ብለዋል።
የሰው ተኮር መርሐ ግብሮችን አጠናክሮ መቀጠል፣ የአመጋገብ ባህል እንዲሻሻል መጣርና የምርት አማራጮችን ማስፋት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር መልካም ጅምሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥልቀት በማየት በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የብድር ሁኔታን የማመቻቸት፣ የስልጠና ዕድሎችን የማስፋትና የሰዎች የአስተሳሰብ በመለወጥ ረገድ እንዲሁም የመስሪያ እና የመሸጫ ቦታዎችን በአግባቡ ጥቅም ለማዋል አመራሩ በትኩረት እንዲሰራበት አስገንዝበዋል።
ከተረጅነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ከቤተሰብ እቅድ ጀምሮ የድጋፍና ክትትል ስራን በማጠናከር ከሌማት ትሩፋትና ሌሎች የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ኢኒሼቲቮች ትግበራ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲፈጠር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠትና ዘላቂ መፍትሄ ለመሻትም የመጠባበቂያ ክምችትን ማሳደግና ጠንካራ የአሰራር ስርአት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በጥንቃቄ በመለየት ለፈጣን ምላሽ፣ በቂና የተሟላ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።