የታክስ አስተዳደርን ለማዘመን የተጀመሩ ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ይተገበራሉ – ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በ2018 በጀት ዓመት የታክስ አስተዳደርን ዘመናዊ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ይተገበራሉ አሉ።
ሚኒስትሯ በ2018 ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ላይ ባደረጉት ገለጻ፤ በበጀት ዓመቱ ጠቅላላ የመንግስት ገቢ 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ሆኖ ታቅዷል።
ይህንን ገቢ ለማሰባሰብ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቅሰው፤ የመካከለኛ ዘመን የገቢ ስትራቴጂ አተገባበር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የታክስ ኦዲትና የታክስ ተገዢነት ሥራ እንደሚጠናከር፣ የንብረት ታክስ ተግባራዊ እንደሚሆን እንዲሁም እየጨመረ የመጣው የክልሎች የገቢ ማሰባሰብ አቅም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ዲጂታል ስርዓቶች እንደሚጠናከሩም ተናግረዋል።
ከአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ጋር ተያይዞ የሚተገበረው የዝቅተኛ አማራጭ ገቢ በታክስ አሰባሰብ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የኤክሳይዝ ታክስ ዘመናዊ ቴምብር ስርዓት እና የቅድሚያ ግብር ምጣኔ ማሻሻያ ለበጀት ዓመቱ የገቢ ዕቅድ መሳካት ትልቅ መነሻ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በዚህም በ2018 በጀት ዓመት የመንግስት ገቢ 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር እንዲሆን መታቀዱን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 1 ትሪሊየኑ የታክስ ገቢ ነው ብለዋል።
ታክስ ካልሆነ ገቢ 129 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን በማንሳት፤ ገቢው ተቋማት አገልግሎት በመሸጥ የሚያመጡት በመሆኑ አገልግሎታቸውን ማዘመን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የመንግስትን የወጪ ዕቅድ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ የተለያዩ ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ 1 ነጥብ 928 ትሪሊየን ብር በጀት ተይዟል ነው ያሉት።
በዚህም የመካከለኛ ዘመን የልማት ኢንቨስትመንት፣ የውጭ ምንዛሪ ሪፎርም የፊስካል አንድምታ እንዲሁም የካፒታል ወጪ ነባር ፕሮጀክቶች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑ ታሳቢ ተደርጓል ብለዋል።
ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በራሳቸው አቅም ወጪያቸውን መሸፈን፣ የአስተዳደር ወጪዎች ውጤታማነት ቁጠባ፣
በዲጂታላይዜሽን የተደገፈ አስተዳደርና ግዢ እንዲሁም ተጋላጭነት፣ ድጎማ እና መልሶ ማቋቋም ታሳቢ ስለመደረጋቸው ተናግረዋል።
ውጤታማ የበጀት ጉድለት አሸፋፈን እና አማራጭ ፋይናንስ ማስፋትም ከግምት ውስጥ መግባታቸውን አብራርተዋል።