በፍትሕና ዳኝነት ዘርፍ በተሰሩ የሪፎርም ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ማጠናከር ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፍትሕ እና ዳኝነት ዘርፍ በተሰሩ የሪፎርም ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕንጻ እና የዲጂታላይዜሽን ምረቃ ሥነ ሥርዓት በባሕርዳር ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሥራ ከባቢ ዕድሳት እና ዲጂታላይዜሽን ማስጀመሪያ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ውጤት ነው።
የሥራ ከባቢው ማማር ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓትም የተዘረጋለት ተቋም መሆኑን ጠቁመው÷ የፍርድ ቤቱ ለውጥ በሌሎች ተቋማት በአርአያነት የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡
በዳኝነት እና በፍትሕ ዘርፉ በተሰሩ የሪፎርም ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች ቢኖሩም ያልተሻገርናቸው ብዙ የፍትሕ አገልግሎት ጥያቄዎች አሉ ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በዚህ ምክንያት እንደ ሀገር ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተዘጋጅቶ በፌደራልና በክልል የፍትሕ አካላት እየተተገበረ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ፍርድ የሚሰጥበት እና እህል የሚቀመጥበት ቦታ ከፍ ማለት አለበት ለሚል የአማራ ሕዝብ ተገቢ የተቋም ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የባለ አራት ወለል ሕንጻ መሰረታዊ ዕድሳት፣ ባለ 3 ወለል አዲስ ሕንጻ ግንባታ፣ ባለ አንድ ወለል መካከለኛ ሕንጻ ግንባታን እና የፍ/ቤቶች የመጀመሪያው ዙር የዲጂታላይዜሽን ሥራ በስኬት አጠናቅቋል ብለዋል፡፡
ሕንጻው የመገልገያ ቢሮዎችን፣ የችሎት አዳራሾችን፣ የተለያየ መጠን ያላቸው የስብሰባ አዳራሾችን፣ የሕጻናት ማቆያ፣ የክልሉን የፍትሕ ሙዚዬም፣ ታዲጊዎች ስለ ፍትሕ ሥርዓት የሚማሩበት ምስለ ችሎት እና ሌሎች ክፍሎችን ያካተተ ነው፡፡
የዲጂታላይዜሽን ሥራው የፍ/ቤቱ ባለድርሻ ተቋማት እና ተገልጋዮች በየአካባቢያቸው ሆነው የፍ/ቤት ጉዳያቸውን መከታተል የሚችሉበት እንዲሁም ጊዜን፣ ወጪን እና እንግልትን የሚቀንስ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በለይኩን ዓለም