በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ተሸፍኗል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 41 ሺህ 394 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለምቷል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።
በቢሮው የመስኖ ልማት ዳይሬክተር እስራኤል እዮብ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ በበጋ መስኖ 65 ሺህ 347 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 41 ሺህ 394 መሬት ማልማት ተችሏል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነት በክልሉ እያደገ በመምጣቱ እስካሁን 491 ሄክታር መሬት በማልማት ምርት የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ሌሎች በአካባቢው የሚመረቱ የአትክልት ምርቶችን በማምረት ለገበያ እየቀረበ መሆኑንም አስረድተዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ ሦስት አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቀው ለልማት ዝግጁ መደረጋቸውን ገልጸው÷ በመስኖ ልማት ከ63 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር በርካታ ስራዎች በመሰራታቸው የአርሶ አደሮች ምርታማነት መጨመር መቻሉን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም በክልሉ ካለው የመብራት ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ የሶላር ፓምፖችን አርሶ አደሮች መጠቀም እንዲችሉ መደረጋቸውን አንስተዋል።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ 15 ሚሊየን በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ጠቀሰው÷ እስካሁን 5 ሚሊየን 733 ሺህ 254 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አመልክተዋል።
በሶስና አለማየሁ