Fana: At a Speed of Life!

በአለልኝ አዘነ ግድያ ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች በጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀድሞው የባህር ዳር ከተማ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች አለልኝ አዘነ ግድያ ጥፋተኛ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በ16 እና 15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤት ወሰነ፡፡

የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ተከሳሽ የአለልኝ አዘነ ባለቤት ወ/ሮ አደይ ጌታቸው ድርጊቱን በመላ ሃሳቧና አድራጎት በወንጀሉ ድርጊትና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን ድርጊቱን የራሷ በማድረግ እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ የወ/ሮ አደይ ጌታቸው እህት ባል የሆነው ሉንጎ ሉቃስ በቀጥታ ወንጀሉን በመፈፀም የተሳተፈ በመሆኑ በፈፀሙት ታስቦ በሚፈፀም ተራ የሆነ ሰው መግደል ወንጀል ተከስሰዋል፡፡

ተከሳሾቹ መጋቢት 17/ 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ 5፡30 እስከ 8 ሰዓት ገደማ ባለው ጊዜ በአርባ ምንጭ ከተማ ነጭ ሳር ቀበሌ ልማት ሰፈር በተቀነባበረ ሁኔታ የ26 አመቱን ወጣት አለልኝ አዘነን በመግደል ራሱን ያጠፋ እንዲመስል በማድረግ የግድያ ወንጀል መፈፀማቸው በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች በመረጋገጡ የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔን ማሳለፉ የሚታወስ ነው።

ፍርድ ቤቱ በቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች አለልኝ አዘነ ግድያ ጥፋተኛ በተባሉት 1ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ አደይ ጌታቸው (የአለልኝ አዘነ ባለቤት) ላይ የ16 አመት እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ሉንጎ ሉቃስ (የወ/ሮ አደይ ጌታቸው እህት ባል) ላይ 15 አመት ፅኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

በሲፈን መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.