Fana: At a Speed of Life!

የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓልን በስኬት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓልን በስኬት ለማክበር አስፈላጊ ዝግጅት ተደርጓል አለ የበዓሉ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት።

የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ፓሊስ መምሪያ አዛዥና የበዓሉ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ረዳት ኮሚሽነር ናስር መሀመድ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፥ የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል በስኬት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።

ለዚህም በምስራቅ ቀጣና የሚገኘው የጸጥታ ኃይል በተለይም ከድሬዳዋ፣ ሀረሪ ክልል፣ ሲቲ ዞን፣ ምዕራብ ሀረርጌ እና ማያ ሲቲ እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስና ከሀገር መከላከያ ጋር በመሆን እቅድ በማውጣት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ከሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ለማስቻል በቂ ውይይት ስለመደረጉ ጠቅሰው፥ በመንገድ ትራፊክ ረገድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ዝግጅቶች ተጠናቀው አስፈላጊውን ስምሪት መደረጉን ያነሱት የመምሪያው አዛዥ፥ በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶች የትራፊክ ህግን አክብረው ሊያሽከረክሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ማህበረሰቡ አጠራጣሪ ጉዳዮች በሚያስተውልበት ወቅት ለፀጥታ አካላት በማሳወቅ ለበዓሉ ስኬታማነት ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በተስፋዬ ሃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.