በአረንጓዴ ዐሻራ ከተተከሉ ችግኞች መካከል 27 ነጥብ 5 በመቶ በአባይ ተፋሰስ የተተከሉ ናቸው – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተከለቻቸው ችግኞች መካከል 27 ነጥብ 5 በመቶ ያህሉ በአባይ ተፋሰስ የተተከሉ ናቸው አሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ90 ሺህ እስከ 100 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የሚገኝ ደን ይጨፈጨፍ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይህ የደን ጭፍጨፋ ድርቅ፣ ጎርፍና የተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮች እንዲከሰቱ ምክንያት ሲሆን መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ድርቅ፣ ጎርፍ እና የተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮችን ለመቀልበስ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ መከናወን መጀመሩን ጠቅሰዋል።
መርሐ ግብሩ ተግባራዊ በተደረገባቸው ባለፉት ዓመታት 40 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመው÷ የተገኘው ውጤት የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረገ መሆኑን አውስተዋል።
ባለፉት ዓመታት በተተገበረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን የተናገሩት ሚኒስትሩ÷ ወደ 30 በመቶ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ከተተከሉ ችግኞች መካከል 27 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው በአባይ ተፋሰስ ውስጥ መተከሉንና በዚህም የአባይ ተፋሰስ የእጽዋት ሽፋን ወደ 25 በመቶ አድጓል ነው ያሉት፡፡
በ2018 በጀት ዓመት በመርሐ ግብሩ የሚተከሉ ችግኞችን ጨምሮ እንደሀገር ለመትከል የተያዘውን የ50 ቢሊየን ግብ ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
በተያዘው ክረምትም ተጨማሪ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ሀገራዊ ግብ ተይዞ በይፋ ተከላ መጀመሩን አንስተዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ የአፈር መሸርሸርን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ እንዲሁም ለም አፈር በውሃ እንዳይወሰድ ትልቅ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው።
ከእርሻ ማሳ ላይ በየዓመቱ 130 ቶን አፈር ይሸረሸር እንደነበር ጠቁመው÷ በተሰሩ ሥራዎች የሚሸረሸረውን የአፈር መጠን ከነበረበት ወደ 50 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ከማድረግ ባለፈ ደርቀው የነበሩ የውሃ አካላት መልሰው እንዲጎለብቱ እያገዘ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡