Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ምገባ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በኋላ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ምገባ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት እየሰራች ነው አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፡፡

ሚኒስትሩ በ2ኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በትምህርት ቤት ምገባ ላይ የሚደረግን ኢንቨስትመንት አስመልክቶ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮ አቅርበዋል።

በትምህርት ቤት ምገባ አማካኝነት የተመጣጠነ ምግብ ለህጻናት ማቅረብ በተባበሩት መንግስታት የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦች ከተቀመጡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል።

ከምግብ ሥርዓት ጋር በተገናኘ ሀገራት በትምህርት ቤት ምገባ እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራት ላይ ኢትዮጵያ ያሳየቻቸውን ለውጦችና ሂደቶችም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ በትምህርት ቤት ምገባ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ካደረጉ ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፥ በዕቅዱ መሰረት በ2030 ሁሉንም የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በመመገብ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው ብለዋል።

መንግስት ዕቅዱን ለማሳካት የትምህርት ቤት ምገባን በበጀቱ ውስጥ በማካተት እየሰራ ሲሆን ክልሎችም አላማውን በመረዳት ትኩረት እንደሰጡት ተናግረዋል።

የትምህርት ቤት ምገባ ቀጣዩ ትውልድ የሚቀረጽበት እንዲሁም ከድህነት መውጣት የሚቻልበት መርሐ ግብር እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.