የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ የማውጣት ጥሪ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ የማውጣት ጥሪ ነው አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በሰጡት መግለጫ፥ የዘንድሮው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር መጀመሩን ይፋ አድርገዋል፡፡
የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ጥሪ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ የማውጣት፣ ለእናት ሀገር አስተዋጽኦ የማበርከት ጅማሮ ስምን ለቀጣይ ትውልድ በኩራት የማውረስ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ጥሪ በዋዛ ሊታለፍ የማይገባው ልዩ የህይወት አጋጣሚ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ኢትዮጵያውያን በዕለቱ በተዘጋጁት የመትከያ ስፍራዎች በመገኘት ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ሌላ አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ዘንድሮ የራሳችንንን የአረንጓዴ አሻራ ክብረ ወሰን በማሻሻል በአንድ ጀንበር 700 ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ ነው ያሉት፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ስራን ማጠናከር፣ የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት፣ ግድቦችን ከደለል መጠበቅና ለዓለም ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ከአረንጓዴ አሻራ ዋና ዋና ግቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በዚህ ዓመት መንግስት ህዝብን በማስተባበር በሰራቸው ስራዎች ሀገራችን ወደ ቀጣዩ የዕድገት ጎዳና እንድትገባ የሚያደርጉ መደላድሎች ተፈጥረዋልም ነው ያሉት፡፡