Fana: At a Speed of Life!

የአፋር ክልል ምክር ቤት 7 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ የቀረበለትን የ2013 በጀት አጸደቀ

አዲስ አበባ ፣ነሀሴ 7 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን አስረኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2013 ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኖ የቀረበለትን የ2013 በጀትና የተለያዩ ሹመቶችን አጸደቀ።

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሃሰን÷ የክልሉን የ2012 ዓ.ም የስራ አፈጻጸምና ተያያዥ ወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ በጀቱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።

“በጀቱ ከ2012 በጀት አመት ጋር ሲነጻጸር በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው” ብለዋል ።

የበጀት ምንጩም ከፌዴራል መንግስት ግምጃ ቤት፣ ከክልሉ ገቢ፣ ከውጭ እርዳታ የሚሸፈን መሆኑን አብራርተዋል ።

በጀቱ በዋናነት በክልሉ የድርቅ ተጋላጭነት ለሚቀንሱ የማህበራዊና የኢኮኖሚ መሰረተ-ልማቶች ማስፋፊያና ለልማት ስራዎች ማስኬጃ የሚውል መሆኑን ገልጸዋል ።

በክልሉ በ2013 በጀት ዓመት ለተለያዩ የልማት ስራዎች ማስፈጻሚያ በቀረበው በጀት ላይ ውይይት ተደርጎ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል ።

የምክር ቤቱ አባላት በጀቱ ከብክነት በጸዳ መልኩ የህብረተሰቡን ችግር ለሚፈቱ ስራዎች በአግባብ እንዲውል አሳስበዋል ።

የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ÷ ወቅታዊ ሀገራዊ የለውጥ ጅምሮችን ጫፍ ለማድረስ የተሻለ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ያላቸው አመራሮች ክፍተት በታየባቸው ቦታዎች የአስፈጻሚ አካላት መተካትና ሸግሽግ ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በርዕሰ መስተዳድሩ የቀረበውን የካቢኔ አባላት ሹመት በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል።

በዚህም መሰረት፡-

አቶ ኢለማ አቡበከር- የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድርና ውሃ ሃብት ቢሮ ኃላፊ
አቶ መሃመድ ጠይብ – የጤና ቢሮ ኃላፊ
አህመድ መሃመድ ቦዳ – የትምህርት ቢሮ ኃላፊ
አቶ ጠሐ አህመድ – የመንግድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙ
አቶ ኢብራሂም ሁመድ – የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ
አቶ መሀመድ ኡዳ – የገጠር መሬት አስተዳደርና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ
አቶ መሃመድ አሊ – የኪል በቲ-ረሱ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዲሁም አህመድ ኢብራሂም የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸው ተገልጿል።

ዛሬ ማምሻውን እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የምክር ቤቱ ጉባኤ የዞን ዳኞችን ሹመትና አዋጆችን እንደሚያጸድቅ ለጉባኤው ከወጣው መርሀ ግብሩ ለማወቅ መቻሉን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.