የሞጆ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታ በቀጣዩ ዓመት ይመረቃል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሞጆ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታን በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ወራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ሞጆን ሁለን አቀፍ የሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው፡፡
የሞጆ ደረቅ ወደብን በቴክኖሎጂ የታገዘና ዘመኑን የዋጀ ሁለገብ የሎጅስቲክስ ማዕከል ለማድረግም የማስፋፊያ ግንባታ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የሞጆ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ አሁን ላይ ወደቡ ያለውን አቅም ከእጥፍ በላይ ማሳደግ እንደሚያስችል ነው የተናገሩት፡፡
ከውጪ ከሚገባው እቃ 90 በመቶው በሞጆ ደረቅ ወደብ እንደሚስተናገድ ጠቁመው ፥ የወደቡን አሰራር በማዘመን የወጪና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ የማስፋፊያ ግንባታው እየተገባደደ እንደሚገኝ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ÷ የማሽነሪ ተከላ ሥራው በቅርቡ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል፡፡
የሞጆ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከል ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ጌታሁን (ኢ/ር) በበኩላቸው ÷ፕሮጀክቱ የኢትዮ ጅቡቲን የንግድ ኮሪደር አቅም ከ95 በመቶ በላይ መሸከም እንዲችል ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ አሁን ላይ 90 በመቶ የደረሰ ሲሆን ÷ በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ወራት ላይ ለማስመረቅ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ