ከውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ የሚያስተላልፉ ወኪሎች ይፋ ሆኑ
ከውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ የሚያስተላልፉ ወኪሎች ይፋ ሆኑ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቀማጭነታቸውን አሜሪካ ያደረጉና በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ የሚያስተላልፉ የሃዋላ ተቋማትን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
ባንኩ ፈቃድ ያላቸውና ቁጥጥር የሚደረግባቸውን የገንዘብ ማስተላለፊያ መንገዶች መጠቀም ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና ለአሸባሪዎች የሚደረግ ድጋፍን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።
በአንጻሩ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ታማኝነት ለመቀነስና የገበያ ምንዛሪ ዋጋን ለማዛባት በማለም በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩ መኪሎች መኖራቸውን አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በውጭ ሀገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ አባላት የተሰበሰበን ገንዘብ ሕገ ወጥ ተግባርን ለመደገፍ የሚውሉና ገንዘብ በማሸሽ ተግባር ላይ የተሰማሩ አስተላላፊዎች መለየታቸውን ነው ያስገነዘበው፡፡
በዚህ መሰረትም፡-
1. ሽገይ የገንዘብ ማስተላለፊያ ወኪል ( Shgey Money Transfer)
2. አዱሊስ የገንዘብ ማስተላለፊያ ወኪል (Adulis Money Transfer) USA)
3. ራማዳ ፔይ (Ramada Pay (Kaah)
4. ቲኤኤጄ የገንዘብ ማስተላለፊያ ወኪል (TAAJ Money Transfer)
የተሰኙ የሃዋላ ተቋማት ከውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ እንደሚያስተላልፉ ተጠቁሟል፡፡
የወኪሎችን እንቅስቃሴ ለመመርመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን የጠቀሰው ባንኩ ÷ ምርመራውን አጠናክሮ በመቀጠል ተገቢ ርምጃ እንደሚወስድ አስገንዝቧል፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ፈቃድ በሌላቸው የገንዘብ ማስተላለፊያ ወኪሎች ገንዘባቸውን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ከመላክ እንዲቆጠቡም አሳስቧል፡፡
በእነዚህ ወኪሎች በኩል የተላከ ገንዘብ ሊወረስ እንደሚችል እና ከተላከ በኋላ ለተፈለገው አካል ስለመድረሱ ምንም አይነት ዋስትና እንደሌለም አመልክቷል።
በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ እና አስተማማኝ መንገዶችን በመጠቀም ገንዘባቸውን እንዲጠብቁም አስገንዝቧል፡፡
ሕጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ወኪሎችን ሙሉ ዝርዝር ከታች በተቀመጠው የብሔራዊ ባንክ ድረ ገጽ ላይ ማግኘት እንደሚቻልም ባንኩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡