ክረምትና የከሰል ጭስ…
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ክረምቱን ተከትሎ ከሚመጣው ቅዝቃዜ ጋር ተያይዞ የሰዎች የከሰል አጠቃቀም ከወትሮው በተለየ መልኩ ይጨምራል፡፡
በርካቶች በክረምት ወቅት በቤታቸው የሚኖርን ቅዝቃዜ ለመከላከል ከሰልን ሙቀት ለመፍጠር ሲጠቀሙ በስፋት ይስተዋላል፡፡
በሌላ በኩል በክረምቱ በዝናቡ ማየል ሳቢያ በሚኖር የመብራት መቆራረጥ፣ ቡና ማፍላትን እና በተለያዩ ምክንያቶች ከሰልን ከቤታቸው የማይለዩ ብዙዎች ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ቤታችንን ለማሞቅ የምንጠቀምበት ጭስ በአግባቡና በጥንቃቄ ካልተያዘ ሕይወትን እስከማጣት የሚደርስ አደጋን ሊያስከትል ይችላል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንደሚሉት÷ ክረምት በመጣ ቁጥር ስጋት ከሚባሉት መካከል የከሰል ጭስ አንዱና ዋነኛው ነው።
ከሰል በውስጡ ካርበን ሞኖ ኦክሳይድ የተባለ መርዛማ ጋዝ በውስጡ መያዙን ጠቁመው ÷ ይህም ለሰው ልጆች ሕይወት አደገኛ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል ።
በርካቶች በክረምት ከሰልን ምርጫ ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞ በተለየ ሁኔታ በዚህ ወቅት በከሰል ጭስ የመታፈን አደጋ ጎልቶ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡
ይህ አደጋ የሚከሰተው ጭሱ ያላለቀ ከሰልን ወደ ቤታችን ውስጥ በምናስገባበት ወቅት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ገለጻ÷ጭሱ ያላለቀለት ከሰል በውስጡ ከፍተኛ ካርበን ሞኖ ኦክሳይድ በመያዙ በቤታችን ውስጥ አየር የማይገባ ከሆነ ቀስ በቀስ ይህ መርዛማ ጋዝ የቤታችን አየር በመቆጣጠር ለአደጋ ያጋልጠናል።
ካርበን ሞኖ ኦክሳይድ ወደ ውስጣችን በምንስብበት ወቅት በቀጥታ በደማችን ውስጥ በመግባት ቀይ የደም ሕዋስ አካል የሆነውንና ኦክስጅን ተሸክሞ ለተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች የሚያደርሰውን አካል ይጎዳዋል ነው ያሉት።
በዚህም ምክንያት ደማችን ኦክስጅን መሸከሙን ስለሚያቆም ሕዋሳቶቻችንና የሕዋሳቶቻችን አነስተኛ ክፍሎች ቀስ በቀስ ወደ ሞት እንደሚሄዱ አስረድተዋል።
ከከሰል የሚወጣው ካርበን ሞኖ ኦክሳይድ የተባለው ጭስ በአይን የማይታይና ሽታ አልባ በመሆኑ ዝምተኛው ገዳይ የሚል ስያሜ እንዳለውም ለፋና ዲጂታል አብራርተዋል።
በባለፈው ዓመትም በዚህ የከሰል ጭስ መታፈን አደጋ የሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውሰው÷ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አቶ ንጋቱ ከሰልን አቀጣጥሎ ወደ ቤት ከማስገባት በፊት ጭሱ ወጥቶ ፍም እስኪሆን መጠበቅ የከሰል ጭስ አደጋን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ አመልክተዋል።
ወደ ቤት ከገባ በኋላም በርና መስኮትን በመክፍት አየር እንዲገባ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ