Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን ይጠበቃል አለ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት የሚኖረውን የአየር ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው ባለፉት ሁለት ወራት የነበረው የዝናብ መጠን ከመደበኛው በላይ በአማካይ ከ30 እስከ 120 ሚሊ ሌትር እንደነበር ጠቅሰው፥ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ሆኖ መመዝገቡን ተናግረዋል።

ይህን የአየር ጸባይ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተደረገ የትንበያ ግምገማ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እንደሚኖር ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

ለመኸር ሰብል አምራች፣ ርጥበት አጠር ለሆኑ አከባቢዎች የአየር ሁኔታው በጎ ዕድል ይዞ እንደሚመጣም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ለመስኖና ለኤሌክትሪክ ኃይል የሚውሉ ግድቦች ክምችታቸው ከፍ እንዲልና ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።

የአፈር ውስጥ ርጥበት መብዛት፣ በእርሻ ማሳዎች ላይ ውሃ መተኛት በግብርና ስራዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ገልጸው፥ ለዚህ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የግብርና ባለሞያዎችን ምክረሃሳብ እንዲተገብሩ አስገንዝበዋል።

ከዚህ ባለፈ የአፈር መሸርሸርና የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሥፍራዎች ጉዳት ሊደርስ ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

በወንድሙ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.