Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን እንደማይጎዳ ሊታወቅ ይገባል – አቶ ሙሳ ሼኮ

‎‎አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሀገርን ጥቅም ከማስከበር አንፃር በአረቡ ዓለም ትላልቅ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ስለ ኢትዮጵያ ከሚሟገቱ ኢትዮጵያውያን መካከል አቶ ሙሳ ሼኮ አንዱ ናቸው፡፡

ከሰሞኑም ኳታር ዶሃ በሚገኘው የአልጃዚራ ጣቢያ በመገኘት በግድቡ ዙሪያ ሰፋ ያለ ቆይታ ያደረጉ ሲሆን÷ በቆይታቸውም ግድቡ ከጥንስሱ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለፈበትን ሂደት በተመለከተ አስረድተዋል፡፡

በተለይም ግድቡ የመላው ኢትዮጵያውያን ህልም ስኬት መሆኑን በማውሳት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ሰበብ ከግብፅ በኩል የሚቀርብባትን መሰረተ ቢስ ውንጀላና አሉባልታ አጣጥለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2011 ግብፅ ያጋጠማትን አለመረጋጋት ተጠቅማ ቀደም ብለው የተፈረሙ ስምምነቶችን በመጣስ በአንድ ወገን ውሳኔ ግድቡን ሰርታለች፤ ለድርድርም ፍቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች በሚል የሚቀርበውን ክስ ውድቅ አድርገዋል፡፡

አቶ ሙሳ በተለይም ግድቡን የመገንባት መሻትና ዕቅድ ግብጽ እንደምትለው ውስጣዊ አለመረጋጋቶቿን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የተጀመረ ሳይሆን ቀደም ባሉት ዘመናት ጀምሮ የነበረ ውጥን ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

ግድቡን ለመስራት ሃሳብ የተጀመረው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ ኢትዮጵያ ከግዛቷ የሚመነጨውን የዓባይን ውሃ ለመጠቀም እቅድ እንደነበራትና በሂደት “የህዳሴ ግድብ” ወደሚል ሀገራዊ ፕሮጀክት ማደጉን ታሪክን ዋቢ አድርገው ሞግተዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን ስትገነባ ከግብፅና ሱዳን ጋር በፈረንጆቹ 2015 የመግባቢያ ስምምነት ተደርሶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሙሳ፥ ሆኖም ግብፅ በተለያዩ ጊዜያት ድርድሩን አረብ ሊግን ጨምሮ ወደተለያዩ አካላት በመውሰድ እንዲወሳሰብ ስታደርግ ቆይታለች ነው ያሉት፡፡

ከዚያም አለፍ ሲል ኢትዮጵያ የስምምነቱ አካል ባልሆነችበት የቅኝ ግዛት ዘመን ውል መሰረት አስገዳጅ ስምምነቶችን እንድትፈርም ስትጥር እንደቆየች አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የግብፅን የአባይ ውሃ ድርሻ ልትገድብ ትፈልጋለች በሚል በግብፅ ሚዲያዎች የሚሰራጩ አሉባልታዎች እንደሚያስገርማቸውም አቶ ሙሳ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወንዙ የሚመነጨው ከግዛቷ በመሆኑ የመጠቀም መብት እንዳላት ጠቅሰው፥ ነገር ግን ግብፅን ወይም ሱዳንን የመጉዳት ምንም ፍላጎት እንደሌላት አስረድተዋል፡፡

በዚሁ የቴሌቪዥን ውይይት ላይ የግብጹ የብሔራዊ ደህንነትና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አማካሪ ሜጀር ጀነራል መሀመድ አብደል ዋሂድ፥ “ኢትዮጵያውያን በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለግብፅ ያላቸው አመለካከት የጠላትነት ነው” በማለት ለሰጡት የተሳሳተ አስተያየትም አቶ ሙሳ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ጠቃሚ መንፈሳዊና ታሪካዊ ግብአት አድርገው የሚመለከቷቸው የግብፅ የሃይማኖት ተቋማትንና መሰረቶችን በመጥቀስ፥ ለግብጻውያን ትልቅ ክብር እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

ግድቡን በሚመለከት ለ14 ዓመታት ስምምነት ላይ ሳይደረስበት ለዘለቀው ድርድር ውድቀት ዋና ምክንያት ግብፅ ታሪካዊ ድርሻ በሚል አባዜ መጠመዷ ነው ብለዋል፡፡

ግብፅ የግድቡን ግንባታም ሆነ የኢትዮጵያን የውሃ አጠቃቀም እንደማትቃወም ስትገልጽ ብትደመጥም፥ ቀድሞ የነበረው የውኃ አጠቃቀም እንዲቆይ መፈለጓ የክርክሩም መነሻ መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን የሴራ ሃሳቦችን አናራምድም ግብፅን ወይም ሱዳንን ለመጉዳት ውሃ የመቁረጥ አላማ የለንም ያሉት አቶ ሙሳ፥ የግድቡ ዋና ዓላማ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የህዝቡን ፍላጎት ማሟላትና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለማድረሱን ገልጸው፥ ግብፅ ከተራ ክስ ባለፈ የደረሰባትን ጉዳት የሚያረጋግጥ ምንም አይነት ይፋዊ ማስረጃ የላትም ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግብፅ እና ሱዳንን ጨምሮ የተፋሰሱ ሀገራት መሪዎች በግድቡ ይፋዊ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲታደሙ ግብዣ ማቅረባቸው የኢትዮጵያን በጋራ የመልማት መልካም ሀሳብ የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል።

የግድቡን አሞላል ሂደት አስመልክቶ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን የተጋነነ መረጃ በማቅረብ የህዝቡን አመለካከት በአሉታዊ መንገድ በመቅረጽ ዘመቻ ተጠምደዋል ነው ያሉት፡፡

ግድቡ ህጋዊ አይደለም የሚለው የግብፅ ባለስልጣናት ክስ ለድርድር ሂደት የማይጠቅም መሆኑን ገልጸው፥ መፍትሄው በውይይትና በመግባባት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሁሉንም ወገኖች ጥቅም የሚያረጋግጥ ፍትሃዊ ስምምነት እንዲኖር እንደምትሰራ አረጋግጠዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በግድቡ ላይ ለ13 ጊዜ ያህል መወያየቱን አስታውሰው፥ ነገር ግን በኢትዮጵያ ላይ ምንም አይነት የውሳኔ ሃሳብ አለማሳለፉ ፕሮጀክቱ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለበት አመላካች ነው ብለዋል፡፡

ግብፅ እና ኢትዮጵያ በአጋርነት እንደሚሰሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ለአካባቢው ልማት የሚያገለግል የተቀናጀ ፕሮጀክት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በአህመድ አብዱልባር

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook WMCC
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.