Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ‘የብርሃን ገበያ’ ማዕከል ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል 10 ሺህ ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ‘የብርሃን ገበያ’ ማዕከል ይፋ ሆኗል።

የመጀመሪያው ዙር የወጣቶች የ”ብርሃን ገበያ” ማዕከል መክፈቻ መርሐ ግብር ዛሬ በአምቦ ከተማ የተካሄደ ሲሆን÷ በከተማዋ ተደራጅተው 23 ሱቅ የተከፈተላቸው 66 ወጣቶች ሥራ ጀምረዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ከድር እንዳልካቸው በወቅቱ እንዳሉት÷ የ”ብርሃን ገበያ” ማዕከል የመንግስትና የግል ዘርፉን አጋርነት በማጠናከር ለወጣቱ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት አካል ነው።

ወጣቱን በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ የብርሃን ገበያ ማዕከል ገበያ በማረጋጋት ለወጣቱ የስራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸዋል።

ሱቅ ተከፍቶላቸው ስራ የሚፈጠርላቸው ወጣቶች በዱቤ የሚረከቡትን ሸቀጥ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ም/ኃላፊው÷ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ክትትልና ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

የብርሃን ገበያ ማዕከል ፕሮጀክትን ከመንግስት ጋር በመተባበር ዕውን ያደረጉት ጢግሮስ፣ ሊንክ አስ እና ኢዩ ሸገር ትሬዲንግ ኩባንያዎች በጋራ በመሆን ወጣቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ፕሮጀክቶች እየሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

ይህንንም ተግባር አጠናክሮ በማስቀጠል በመላ ሀገሪቱ ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራ ነው ያረጋገጡት፡

የሊንክ አስ ትሬዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፊልሞን ካሳሁን በበኩላቸው÷የገበያ ማዕከሉ ምርት በማቅረብ በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

የጢግሮስ ትሬዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኔ ጌታቸው ÷ ብርሃን ገበያ ወጣቶችን የአነስተኛ ሱፐር ማርኬት ባለቤት የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።

አነስተኛ ሱፐር ማርኬቶቹን በአምስት ዓመት ውስጥ ወደ ከፍተኛ የገበያ ማዕከላት የማሳደግ የስራ ዕቅድ ተይዟል ነው ያሉት።

በተለያዩ ከተሞች ለወጣቶች ስልጠና በመስጠት ያለ ምንም መነሻ ወደ ስራ የማስገባት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

ከቻይና የሚመጡ እና በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ሸቀጦች ለወጣቶቹ በዱቤ የሚቀርብላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ኩባንያዎቹ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ፕሮጀክቱን ይፋ አድርገው በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር መሸጋገራቸውን ጠቁመው÷ በቀጣይ ፋርማሲዎችን ጨምር ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ማዕከላት እውን እንደሚደረጉ ጠቅሰዋል።

ይህንን ዓላማ ለማሳካት ብርሃን ገበያ ከዳሽን ባንክ፣ ከስንቄ ባንክ፣ ከኢንሳ እና ከሌሎችም መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ይሰራል ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.