Fana: At a Speed of Life!

10 ክልሎች መደበኛ የሰብአዊ ድጋፍን በራሳቸው ማሟላት ችለዋል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ተረጂነትን ለማስቀረት በተከናወኑ ተግባራት 10 ክልሎች የትኛውንም ዓይነት መደበኛ የሰብአዊ ድጋፍ አገልግሎት በራሳቸው ማሟላት ችለዋል አሉ።

የአደጋ ስጋት አመራር ጉዳዮች የብሔራዊ ደህንነት፣ የሰብዓዊ መብትና የማህበራዊ ፍትህ አጀንዳዎች መሆናቸውን ያብራሩት ኮሚሽነሩ፤ በተጨማሪም የሰላም ግንባታ እና የዘላቂ ልማት ማረጋገጫ ተደርገው ይወሰዳሉ ነው ያሉት።

በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮች በአንድ ላይ ቀምሮ ለመስራት የአደጋ ስጋት አመራር ስራን በተጠናከረ መልኩ ማከናወን በዘርፉ ተጨማሪ አቅምና ስኬትን ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ያከናወነችው ተግባር የሚበረታታና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመው፤ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ስርዓት ጉባኤን በተሳካ ሁኔታ ማካሔዷ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍ ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት 10 ክልሎች የትኛውንም ዓይነት መደበኛ የሰብአዊ ድጋፍ አገልግሎት በራሳቸው በማሟላት ላይ መሆናቸው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ቀደም ሲል ለሰብዓዊ ድጋፍ ተብሎ ከውጭ ይገባ የነበረውን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት በራስ አቅም መሸፈን መቻሉንም አብራርተዋል።

ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሂደት ትልቁ ማንሰራራት በሚል የተመዘገበ ስኬት መሆኑን ገልጸው፤ ከሶስት ዓመት በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበረውን የተረጂዎች ቁጥር በ86 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል።

ይህም የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን እንደሚያረጋግጥ አብራርተዋል።

በክልሎች ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 100 ሺህ ሔክታር መሬት መታረሱን ጠቅሰው፤ ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል በዘንድሮ መኸር ወቅት የተሻለ የምርት አቅምን ለመፍጠር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

የአደጋ ምላሽ ፈንድ ማቋቋም፣ የመዋቅር ማሻሻያና የክምችት አቅምን መጨመር ላይ መሰራቱንም ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.