Fana: At a Speed of Life!

የሌማት ትሩፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው – ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በእንስሳት ሃብት ልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው አለ የግብርና ሚኒስቴር ፡፡

የሲዳማ ክልል እንስሳት ሃብት ልማት ንቅናቄና የመኖ ችግኝ ተከላ በዛሬው ዕለት በሸበዲኖ ወረዳ ተካሂዷል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ እንደሀገር የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ባለፉት ሦስት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ውጤት አስገኝቷል፡፡

የእንስሳት ሃብት ልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እያገዘ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ዘርፉ ኢኮኖሚውን በመደገፍና ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተያዘው በጀት ዓመት ከ160 ሚሊየን በላይ የአንድ ቀን ጫጩቶች እንደሚሰራጩ ጠቁመዋል።

5 ሚሊየን የእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና 12 ቢሊየን እንቁላል ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ በዓሣና በማር ምርትም ሰፋፊ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ተጨባጭ ውጤት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት በሀገር ደረጃ ምሳሌ የሚሆኑ ስራዎች መሰረታቸውን ጠቁመው፥ የተገኘውን ውጤት ቀጣይነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

በእንስሳት ሃብት ልማት እየታየ ያለው እድገት ከምርት አቅርቦት ዋጋ ጋር እንዲመጣጠን ለመኖ ልማት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.