Fana: At a Speed of Life!

ብሪታንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ የታዳጊ ሀገራት ምርት አቅርቦት ሰንሰለትን ለመከላከል የሚረዳ የ6 ነጥብ 85 ሚሊየን ፓውንድ የድጋፍ መርሃ ግብር ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪታኒያ መንግስት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመሆን የታዳጊ ሀገራት የምርት አቅርቦት ሰንሰለትን ለመከላከል አዲስ የ6 ነጥብ 85 ሚሊየን ፓውንድ የድጋፍ መርሃ ግብር ይፋ አደረገ፡፡

መርሃ ግብሩ በኮሮና ቫይረስ ወቅት በታዳጊ ሀገራት ውስጥ ያሉ ሠራተኞችን ከመደገፍ አልፎ ብሪታንያ ከሀገራቱ የምታስገባቸው አስፈላጊ ምርቶች ጥበቃ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል፡፡

ከዚህ ባለፈም በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ውስጥ ወደ 1 ሚሊየን የሚጠጉ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸውን ይደግፋልም ነው የተባለው፡፡

ከታላላቅ የንግድ ተቋማት ጋር በመተባበር የሚደረገው ድጋፍ ከአዳጊ ሀገራት ወደ ብሪታንያ የሚላኩ ምርቶች ሰንሰለታቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችል ሲሆን በተቋማቱ ውስጥ የሚሰሩት ሰዎች ደግሞ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ብሪታኒያ 20 በመቶውን የምግብ እና የመጠጥ ምርት ከታዳጊ ሀገራት የምታስገባ ሲሆን በኮሮና በቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አብዛኞቹ ምርቶች የአቅርቦት ሰንሰለታቸው ተጎድቷል፡፡

አዲሱ መርሃ ግብር አትክልት፣ ቡና እና አልባሳት የመሳሰሉ ምርቶች ሰንሰለታቸው ሳይቆራረጥ ወደ እንግሊዝ እንዲገቡ ይረዳል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለመርሃ ግብሩ ከተመደበው ውስጥ 4 ነጥብ 85 ሚሊየን ፓውንዱ ከመንግስት እንዲሁም 2 ሚሊየን ፓውንድ ከንግድ ተቋማት የተገኘ ሲሆን በዋናነት ከኢትዮጵያ፣ ማይናማር፣ ባንግላዴሽ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ ፣ ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ የሚላኩ ምርቶችን ለማሳለጥ እና ሰራተኞችን ለመደገፍ የሚውል ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.