9 ነጥብ 1 ሚሊየን የተሻሻሉ የዓሳ ጫጩት ዝርያዎች…
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት 9 ነጥብ 1 ሚሊየን የተሻሻሉ የዓሳ ጫጩት ዝርያዎች ተሰራጭተዋል አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡
የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የሌማት ትሩፋት ለዓሳ ምርት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
መርሐ ግብሩ ዓሳን ከተፈጥሮ ሐይቆች በተጨማሪ በሰው ሰራሽ ሐይቆች በማምረት ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን አስረድተዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት የዓሳ ምርትን ለማሳደግ 9 ነጥብ 1 ሚሊየን የተሻሻሉ የዓሳ ጫጩት ዝርያዎችን ማሰራጨት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የተሻሻሉ የዓሳ ጫጩት ዝርያዎች በአምስት ማዕከላት መባዛታቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴዔታው ÷ ማዕከላቱ ለዘርፉ እድገት ጉልህ ሚና እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱም በሌማት ትሩፋት በተከናወኑ ሥራዎች 243 ሺህ ቶን ዓሳ ምርት መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡
የዓሳ ምርትን የገበያ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከርም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ