በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚነሽር መስፍን ዓርዓያ (ፕ/ር) በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአጀንዳ ማሳባሰብ ሂደት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው አሉ፡፡
መስፍን ዓርዓያ (ፕ/ር) በትግራይ ክልል እና በዳያስፖራው ማህበረሰብ አካባቢ አጀንዳ ለመሰብሰብ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ የዳያስፖራ አባላት አጀንዳ መሆን ይገባቸዋል የሚሏቸውን ጉዳዮች በማቅረብ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የዳያስፖራ አባላቱ ሀሳባቸውን በበይነ መረብ፣ በፖስታ እንዲሁም በስልክ አማራጮች ማቅረብ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ስለ ምክክርና ውይይት የተሻለ ግንዛቤ እንዳላቸው የሚታሰቡት የዳያስፖራ አባላት፤ ባሉበት ሆነው እርስ በርስ ውይይት በማድረግ አጀንዳቸውን ለይተው እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡
ባለፉት 50 እና 60 ዓመታት ልዩነቶችን በመሳሪያ ለመፍታት የተሄደበት መንገድ የህይወት እና የንብረት ውድመት እንዲሁም የአዕምሮ ስብራት ከማስከተል ውጪ ትርፍ እንደሌለው ታይቷል ነው ያሉት።
ሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርገውን የውይይት መንገድ መከተል እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ልዩነቶችንና ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት አማራጭ የሌለው ብቸኛ መፍትሄ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
በአስከፊ ጦርነቶች ውስጥ ያለፉት ምዕራባውያን ግጭት የማያዋጣ መንገድ መሆኑን ተገንዝበው መሳሪያቸውን አስቀምጠው ልዩነቶቻቸውን በድርድርና በውይይት ፈትተው ላሉበት ብልጽግና መብቃታቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህ መልኩ ሰላምና ልማትን ባረጋገጡ ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው የብሔራዊ ምክክር ሂደት አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በመሆኑም አጀንዳቸውን አሰባስበው ለኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከብሔር፣ ሃይማኖት እና መንግስት ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆኑን ያነሱት መስፍን ዓርዓያ (ፕ/ር)፤ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ማብራሪያ ሲፈልጉ በነጻነት ለኮሚሽኑ ማቅረብ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑም አስፈላጊውን ምላሽና ማብራሪያ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በአቤል ነዋይ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!