Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል 15 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ከ15 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ሆነዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅትም በክልሉ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ አባወራዎችና እማወራዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት አባል መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ የአባላት ቁጥር 16 በመቶ የጨመረ ሲሆን÷ አሁን ላይ ሽፋኑ 80 በመቶ መድረሱ ተጠቁሟል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ክሽን ወልዴ÷ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥራ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡

በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ሃብት ማሰባሰብ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

ከ12 ሚሊየን በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች በጤና ተቋማት ተገኝተው የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውንና ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል።

የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ 52 አዳዲስ የማህበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤቶችን ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት የጤና አመራር ሥርዓት አቅምን በማሳደግና የተቀናጀ አመራር በመፍጠር ውጤታማ የሃብት አሰባሰብ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.