የዩክሬን ፕሬዚዳንት በነጩ ቤተ መንግስት ከትራምፕ ጋር ዳግም ሊገናኙ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ትናንት ዓለም በጉጉት ሲጠብቀው የነበረው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ውይይት ያለ በቂ ስምምነት ተቋጭቷል።
የሁለቱ መሪዎች የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት እልባት ያገኝ ዘንድ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል በሚል ሲጠበቅ ነበር።
ሶስት ሰዓት የፈጀው የአላስካ ውይይት ይህ ነው የሚባል የመፍትሄ ተስፋ ሳይፈነጥቅ መቋጨቱን ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ አቅንተው ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ሊወያዩ እንደሆነ ተነግሯል።
ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ጋር ፊት ለፊት ያደረጉት ውይይት ስምምነት ላይ ባይደረስበትም ተቀራርቦ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን መሪዎቹ ተስማምተውበታል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውይይቱን አስመልክቶ ትሩዝ በተሰኘው ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ በቀጥታ ወደ ሰላም ስምምነት መግባት እንጂ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሰላም አያመጣም ብለዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ሰላም ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዚዳንቱ÷ ተኩስ አቁም መደረግ እንዳለበት እና እስረኛ በመለዋወጥ ዘላቂ ሰላም ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ከውይይቱ በኋላ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር የጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ጦርነቱን ለማስቆም ፍላጎት እንዳላቸው ከመግለጽ ባለፈ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በዚህ መልኩ ከተጠናቀቀው የሁለቱ መሪዎች ውይይት በኋላ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በመጪው ሰኞ ወደ ዋሽንግተን ያቀናሉ ተብሏል፡፡
ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ ዘለንስኪ ሩሲያ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲደረግ የማትፈቅድ ከሆነ እና ከድርድሩ የምታፈነግጥ ከሆነ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በስልክ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡
ያለ ዩክሬን ተሳትፎ ስምምነት ሊመጣ አይችልም ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ በውይይቱ የተነሱ እያንዳንዱ ነጥቦች ላይ ዩክሬን የመወሰን መብት አላት ማለታቸወን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ