የትግራይ ክልል ለ1 ሺህ 568 ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትግራይ ክልል 1 ሺህ 568 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን የክልሉ ፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
ታራሚዎቹ በይቅርታ እንዲፈቱ የተወሰነው በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል መሆኑን የቢሮው ሃላፊ ተኪኡ ምትኩ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎቹ መካከል 38ቱ ሴቶቸ መሆናቸውንም የቢሮው ሃላፊ ገልፀዋል።
ሃላፊው ታራሚዎቹ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ለኮማንድ ፖስቱ ከቀረቡት 1 ሺህ 704 ታራሚዎች ውስጥ 1 ሺህ 568 የሚሆኑት በይቅርታ እንዲወጡ ተወስኗል ብለዋል።
ቀሪዎቹ 136 ታራሚዎች ደግሞ ከግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ የወንጀል ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ በይቅርታ ውሳኔው እንዳልተካተቱ ጠቁመዋል።
ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ የኮሮና ቫይረስን በመከላከል እና ለበደሉት ማህበረሰብ ዘላቂ ሰላም አጋዥ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
ኮማንድ ፖስቱ በዚህ ዓመት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በመጋቢት እና ሚያዝያ ወር በተመሳሳይ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲወጡ መወሰኑ ይታወሳል።