Fana: At a Speed of Life!

አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
አርቲስት ደበበ እሸቱ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
አርቲስት ደበበ እሸቱ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን÷ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በፊልም እና በጋዜጠኝነት ሙያ በርካታ ሥራዎችን ለአድማጭ ተመልካች አቅርቧል፡፡
ተዋናይ፣ ኮሜዲያን እና አዘጋጅ ሆኖ ለረጅም ዓመታት ያገለገለው አርቲስቱ ÷ በቴአትር መድረኮች በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሥራዎችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡
አርቲስት ደበበ በሀገር ፍቅርና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (በአሁኑ ብሔራዊ ቴአትር) መድረክ ላይ ለበርካታ ዓመታት በተዋናይነትና በአዘጋጅነት አገልግሏል።
አርቲስት ደበበ መጀመሪያ በቴአትር መድረክ የታየው በመንግስቱ ለማ ያላቻ ጋብቻ ሲሆን÷ በመቀጠልም በሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የተለያዩ ሥራዎችን አቅርቧል፡፡
አርቲስቱ ከተሳተፈባቸው ሥራዎች መካከል ያላቻ ጋብቻ፣ ሮሚዮና ዡልየት፣ ጠልፎ በኪሴ፣ ዳንዴው ጨቡዴ ፣ዘ ጌም ኦፍ ቼዝ፣ ኦቴሎ፣ አንድ ዓመት ከአንድ ቀን፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ በቀይካባ ስውር ደባ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ የወፍ ጎጆ ፣ የቬኒሱ ነጋዴ ፣ ማዕበል እና ሌሎች ይገኙበታል፡፡
በተለያዩ ታሪካዊና አዝናኝ ፊልሞች እንዲሁም የቴአትር ሥራዎች አድናቆት የተቸረው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ÷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የክብር ዶክትሬት ተሰጥቶታል፡፡
አርቲስቱ ሀገር ችግር ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ ከፊት በመቆም በርካታ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን ÷ በበጎ ፈቃድ ሥራዎችም ግንባር ቀደም ነበር፡፡
በሌላ በኩል አርቲስት ደበበ እሸቱ በ1995 ዓ.ም በሃገራዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ የምክር ቤት አባል እስከመሆን ደርሷል፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና ለመላው አድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.