ፖለቲካ በጥላቻና ስሜት ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት መመራት አለበት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ ገበያው በግል ጥላቻና ስሜት ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት ሊመራ ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግስት በተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው ዙሪያ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ መጽሐፉ ከዚህ ቀደም በንድፍ ሃሳብ የተነሱ ሃሳቦችን ተቋማዊ ወይም መንግስታዊ ቅርጽ እንዲይዙ ያስችላል፡፡
ቀደምት የኢትዮጵያ መንግስታት የመንግስታቸውን ቅርጽ፣ እሳቤ፣ የሚከወንበትን መንገድ፣ ሊያሳካው የሚፈልገውን ግብና ውጤት በዚህ ደረጃ በሰነድ ሰንደው አስቀምጠው እንደማያውቁ አንስተዋል፡፡
መጽሐፉ ዋና ሃሳብ በንድፍ ሃሳብና በፍልስፍና ትውልድ እንዴት እንደሚገነባ ያሳየው መደመር ተቋማዊ ወይም መንግስታዊ ቅርጽ እንዲይዝ ለማስቻል እንደሆነ አብራርተዋል።
ከዓለም ጋር የት ተላለፍን፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስብራቶቻችን የት ጀመሩ የሚለውን መጽሐፉ ይተነትናል ብለዋል፡፡
ኋላ ለመቅረታችን ምክንያት የሆኑ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው፤ በእኛና በዓለም መካከል የተፈጠረውን ክፍተት እንዴት ልናጠበው እንችላለን፤ ምን አይነት መደመራዊ አካሄዶችን ብንከተልስ ሊጠብ ይችላል የሚለውን ያብራራል ነው ያሉት፡፡
በመጽሐፉ ከተለመደው የመቅዳት አካሄድ በመላቀቅ መደመራዊ ፈጠራ፣ ፍጥነትና የዝላይ መንገዶችን መከተል ይገባል የሚለውን እንደሚዳስስም ጠቅሰዋል፡፡
መጽሐፉ ሃሳቡን ሲያብራራ ከቀደምት መንግስታት ሃሳቦች ጋር ራሱን እንደሚያወዳድርና በንጽጽር የተመረጡ ሃሳቦች ለምን ጥቅም ላይ እንደዋሉ እንደሚያስረዳ ጠቁመዋል፡፡
መደመርን ፍልስፍናው አድርጎ የሚመራ መንግስት ምን አይነት ባህሪያት እንዳሉት እና ስለሚከተለው ስትራቴጂና የሚያስመዘግበውን ውጤት በዝርዝር ያስቀምጣልም ነው ያሉት፡፡
በሀገር ውስጥና በውጪ ስለሚኖረው ግንኙነት እንዲሁም የተሻገረና የዘመነ ገጠርና ከተማ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል እንደሚያስረዳ አንስተዋል፡፡
በመደመር በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም እና ሌሎች ሃብቶች ያሉ እምቅ እድሎችን ለሀገር ጥቅም እንዴት ማዋል እንደሚቻል እንደሚተነትንም ተናግረዋል፡፡
መጽሐፉ ለስኬቶቻችን ወሳኝ ጉዳዮችን ያነሳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በተለይም የፖለቲካ ስክነት ለኢኮኖሚ ስምረትና ለተቋም መሳለጥ ያለውን ሚና በማብራራት ተግዳሮቶችን በሚገባው ልክ እንደሚያስረዳ አመልክተዋል፡፡
ፖለቲካ እንደሸቀጥ የሚሸቀጥበት ሥርዓት ከሃሳብ የራቀ መሆኑን እንደሚያስረዳ ጠቁመው÷ ሊከሰት የሚችልን አደጋና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ላይ የራሱ እይታ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
እንደ ሀገር ሀገራዊ ትርክት መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ ኢትዮጵያን በምንፈልገው ልክ አስቀምጠን ጥቅማችንን ለማስከበር ያለውን ፈተና እና መውጫ መንገዶችን እንደሚያሳይም ጠቅሰዋል፡፡
ፖለቲካ በግል ጥላቻና ስሜት ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት መመራት እንዳለበት አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ሀገራዊ፣ የወል እና አሰባሳቢ ትርክት መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ