Fana: At a Speed of Life!

የሀገር መሪ ለመሆን በተለያዩ ዘርፎች የካበተ ልምድና ተሞክሮ ሊኖር ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መሪ ለመሆን በተለያዩ ዘርፎች እና ደረጃ የካበተ ልምድና ተሞክሮ ያስፈልጋል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግሥት በተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው ዙሪያ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም የኢትዮጵያ ማንሰራራት ጀምሯል፤ ኢትዮጵያ ለመላው አፍሪካውያን የብልጽግና ተምሳሌት ትሆናለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የመሪነትን ሃላፊነት ለመውሰድ ህልመኛ መሆን እንደሚገባ ጠቅሰው÷ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ህልም ያላቸው ሰዎች ሲበራከቱ ከዚያም ውስጥ በርካታ ፍሬያማ ሰዎች ሊገኙ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ህልሙ ግን ባዶ መሻትና ቅዠት ሳይሆን ተጨባጭ እውቀትና ልምድ ላይ ሊመሰረት ይገባል ነው ያሉት፡፡

አንድ ሰው መሪ ለመሆን ሲያስብ ነገሩን በውስጥ ለረጅም ጊዜ ይዞ ራሱን እያዘጋጀ መቆየት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

መሪነት ዝም ብሎ በመመኘት የማይገኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ ህልምን እውን ለማድረግ መትጋት ይገባል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፡፡

እንደ ሀገር ኢትዮጵያን መምራት ስናስብ ብዝሃነትን፣ ሰፊ ሕዝብና ታሪክ እንዲሁም ውስብስብ ችግር ያላት ሃገር መሆኗን መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በተለይ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ታሪኮች መኖራቸውን መረዳትና የጋራ የሆኑ ነገሮችን በማምጣት የወል ትርክት መገንባት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በቀበሌ፣ በኩባንያ እና በመንግስት ተቋማት ውስጥ መሪ ሆነሕ ሳታገለግል ማስተዳደርን መተንተን በቂ አይደለም ነው ያሉት፡፡

ልምድ ነገሮችን በተለያየ አንግል እንድንመለከት ያስችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ስለሆነም መሪነትን ከመፍራት ይልቅ መትጋትና ማሳካት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመቃወም ባለፈ የተሻለ አማራጭ ሃሳብ ሊያመጡ እንደሚገባ ጠቁመው÷ መንግስት ከመሆን በፊት በሁሉም ዘርፍ ዝግጅት ያስፈልጋል፤ ለዚህም ሰፊ ጊዜ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አውድ መቀየሩን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ከዚህ ቀደም በነበረው የፖለቲካ እሳቤ ውጤታማ መሆን እንደማይቻል አስገንዝበዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ሕዝቡም ውጤቱን ቀምሷል፤ይህን ይበልጥ ለማጠናከርም መትጋት ይገባል ብለዋል፡፡

የመሪነት ክብደት፣ ቅለትና ውጤታማነት የሚለካው በግለሰቡ የልምድ እና ዝግጁነት ደረጃ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ማንሰራራት ጀምሯል፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና ጀምሯል፤ኢትዮጵያ ለመላው አፍሪካውያን የብልጽግና ተምሳሌት ትሆናለች ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ሀገራችን የጀመረችውን ትጨርሳለች ፤ ከልመና ትላቀቃለች፤ ልጆቿ ኮራ ብለው የሚንቀሳቀሱበት ፓስፖርት ያላት ሀገር ትሆናለችም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያን ብልጽግና መጠራጠር አያስፈልግም፤ በተግባር እንዲታይ ብልጽግና ፓርቲ በተግባር አበክሮ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.