የጌደብ ወንዝ ድልድይ ለተሽከርካሪ ክፍት ሆነ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከደብረ ማርቆስ – ባሕርዳር በሚወስደው መንገድ የሚገኘው የጌደብ ወንዝ ድልድይ ለተሽከርካሪ ክፍት ተደርጓል አለ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፡፡
አስተዳደሩ ለፋና ዲጂታል እንደገለጸው ÷ በጎርፍ ጉዳት ደርሶበት የነበረውን የጌደብ ወንዝ ድልድይ በተገጣጣሚ ብረት የመገንባቱ ሥራ ተጠናቅቋል፡፡
በዚህም ድልድዩ በዛሬው እለት ነሐሴ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ለተሽከርካሪ ክፍት ተደርጓል፡፡
የጌደብ ወንዝ ድልድይ ነሐሴ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ሌሊት ጮቄ ተራራ ላይ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በደረሰበት ጉዳት ከደብረ ማርቆስ – ባሕርዳር የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ድልድዩ በጎርፍ ምክንያት ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ግንባታው እስኪጠናቀቅ በትዕግስት ሲጠባበቁ ለቆዩ መንገደኞችና አሽከርካሪዎች ምስጋና ቀርቧል፡፡