Fana: At a Speed of Life!

የዋልያዎቹ የቀድሞ ኮከብ ሽመልስ በቀለ…

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከታዩና የራሳቸውን አሻራ ማኖር ከቻሉ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች ሽመልስ በቀለ ነው፡፡

የእግር ኳስ ሕይወቱ በሀዋሳ ኮረም ሜዳ የተጀመረ ሲሆን፥ በክለብ ደረጃም ከሀገር በመውጣት ጭምር ተጫውቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለስ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል ሽመልስ በቀለ ይጠቀሳል፡፡

ከ10 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ያገለገለው ኮከብ በሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከተጫወቱ ጥቂት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡

ሽመልስ በቀለ በብሄራዊ ቡድን ቆይታውና በተለያዩ ክለቦች በየጨዋታው የሚያደርገው እንቅስቃሴ ግሩም በመሆኑ በርካቶች ያደንቁታል፡፡

በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በሚገኙ ክለቦች መጫወት የቻለው የዋልያዎቹ የቀድሞ ኮከብ አብዛኛውን የእግር ኳስ ሕይወቱን ያሳለፈው በግብጽ ሊግ ነው።

ሽመልስ ከሀገር ከመውጣቱ በፊት ለሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቶ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡

ሽመልስ በቀለ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጪ የመጫወት ዕድል ያገኘው በሊቢያ ሊግ ተሳታፊ ለነበረው ኢትሃድ ትሪፖሊ ሲሆን ÷ነገር ግን በክለቡ የነበረው ቆይታ ከአራት ወራት የዘለለ አልነበረም፡፡

በመቀጠልም ወደ ሱዳን በማቅናት በቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሩገር የሚሰለጥነውን የሱዳኑን አል ሜሪክ በሁለት ዓመት ውል የተቀላቀለው ተጫዋቹ÷ በዚያም ከ6 ወራት በላይ መቆየት አልቻለም፡፡

ሽመልስ ወደ ግብጽ በማምራት ለፔትሮጀት፣ ለምስር አልመካሳ፣ ኤል ጉና እና ኤንፒ ተጫውቶ አሳልፏል፤በግብጽ በቆየባቸው ዓመታት ስኬታማ ጊዜን ያሳለፈው በፔትሮጀት ሲሆን ፥ ለክለቡ 123 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡

ከአስር ዓመታት በኋላ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በመቻል ያሳለፈው ተጫዋቹ ፥ አሁን ማረፊያው የቀድሞ የልጅነት ክለቡ ሀዋሳ ከተማ ሆኗል፡፡

የቀድሞ የዋልያዎቹ ኮከብ ሽመልስ በቀለ በ2018 ዓ.ም የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ይጠበቃል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.