የኮሪደር ልማት አሠራር ለመጪው ጊዜ ታላቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሪደር ልማት አሠራር ለመጪው ጊዜ ታላቅ ተስፋ የሚሰጠን ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በአዲስ አበባ በመጀመሪያው ምዕራፍ በአራት ኮሪደሮች ጀምረን በሁለተኛው ምዕራፍ በስምንት ኮሪደሮች ቀጥለናል ብለዋል፡፡
የተጠናቀቀውን እና 12 ነጥብ 74 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ከአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል-ጎሮ-ቪአይፒ ኤርፖርት የኮሪደር ልማት ሥራ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
በኮሪደሩ 29 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ እና 15 ነጥብ 27 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ መሰራቱን ነው ያስረዱት፡፡
ይህ የኮሪደር ሥራ ሰፋፊ የተሽከርካሪ መንገዶችን፣ ከጎሮ እስከ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ መንገድ እንዲሁም በአካባቢው ሰፊ የወንዝ ልማትን ያካተተ ነው ብለዋል።
ሰባት የስፖርት ማዕከላት፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የታክሲ እና አውቶቡስ መናኸሪያዎች፣ ካፌዎች፣ የሕዝብ መጸዳጃዎች እና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች የተካተቱበት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ግንባታዎች ሥራ ፈጥረዋል፤ መገናኛ እና መዳረሻዎችን አስፋፍተዋል፤ የከተማዋን መሠረተ ልማት አጠናክረዋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በሁሉም መስክ ኢትዮጵያ መበርታቷን ቀጥላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ወደ ብልጽግና የምናደርገው ጉዞ አይደናቀፍም ብለዋል፡፡
የእነዚህ ሥራዎች ስኬት ይህንን ያስቻለውን የተለወጠ ርዕይ እና የሥራ ባሕል እንደሚያንጸባርቅ አንስተዋል፡፡
እስካሁን የከተማዋ ግማሽ ያህሉ መለወጡን ጠቁመው÷ የበለጠ ለማሻሻል የምንተጋባቸው አካባቢዎች አሁንም እንደሚቀሩ አመልክተዋል፡፡