ስትሮክ ፋውንዴሽን የህክምና ማዕከል እንዲገነባ ድጋፍ ይደረጋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ስትሮክ ፋውንዴሽን የተሟላ የስትሮክ ህክምና ማዕከል እንዲገነባ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል አሉ።
ፋውንዴሽኑ የተሟላ የስትሮክ ሕክምና ማዕከል ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።
ከንቲባዋ ፋውንዴሽኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ስትሮክ ለማከም ላሳየው ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበው፤ ከተማ አስተዳደሩ ለግንባታ መሬት ከማቅረብ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ በአቅም ማነስ ከሀገር ወጥተዉ ለማይታከሙ ህሙማን እና ቤተሰብ ትልቅ እፎይታ እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡
የስትሮክ ህክምና በሀገር ውስጥ እንዲሰጥ ማድረግ የጤና ቱሪዝምን በማሳደግ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ስትሮክን ለመከላከል የመዲናዋ ነዋሪዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ ማቅረባቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ዘመን ጁንዲ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡