አስከፊ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመዋጋት የለውጥ ርምጃ ያስፈልጋል – ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አስከፊ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመዋጋት አስቸኳይ የለውጥ ርምጃ ያስፈልጋል አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሞሐመድ አሊ ዩሱፍ ጨምሮ የሀገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ እንዳሉት፤ አፍሪካ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ያላት ሚና አነስተኛ ቢሆንም በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ዋጋ እየከፈለች ነው።
በዚህም አፍሪካ ለታዳሽ ቴክኖሎጂ አስፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች ያላት እንደመሆኗ በዓለም የአየር ንብረት ላይ የመሪነት ሚና መጫወት እንዳለባት አስገንዝበዋል።
ሁሉንም ያማከለ እና ፍትሐዊ የሆነ የአየር ንብረት ፖሊሲ እና የገንዘብ ድጋፍ እንዲተገበርም ጥሪ አቅርበዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ በተለይም በአፍሪካ የሚያደርሰው ተጽእኖ አስከፊ በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት አስቸኳይ የለውጥ ርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል።
አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምትሰራቸውን ጅምር ልማቶችን ማፋጠን፣ የስራ ዕድል መፍጠር እና የምግብ ዋስትናን ማጎልበት እንደሚገባ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ጥረት እያደረገች እንደሆነ አንስተው፤ በዘንድሮ ክረምት ብቻ ከ7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2027 የሚካሄደውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የማስተናገድ ፍላጎት እና አቅም እንዳላት አመልክተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በቁርጠኝነት የምትሰራው ኢትዮጵያ በመስኩ ያከናወነቻቸውን ተግባራት የጉባኤው ተሳታፊዎች እንዲጎበኙም ግብዣ አቅርበዋል።
በሶስና አለማየሁ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!