Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ1 ሺህ 500ኛው የመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።

እንኳን ለ1 ሺህ 500ኛው የመውሊድ በዓል አደረሳችሁ፡፡
የታላላቆቻችንን በዓል የምናከብረው የእነርሱን አርአያ ለመከተል ምክንያት እንዲሆነን ነው፡፡ ምን እንደሠሩ? ምን እንዳስተማሩ? ምን እንደገጠማቸው? ፈተናዎችን እንዴት እንዳለፉ? ታሪካቸውን እያነሣን እንማርበታለን፡፡

የመውሊድንም በዓል ስናከብር የነቢዩ መሐመድን (ሰዐወ) ፈለግ እናጠናለን፣ ከሕይወታቸው እንማራለን፤ ፈተናን የተሻገሩበት መንገድ ለእኛ ብርታት ይሆነናል፡፡ አስተምህሯቸውን እያስታወስን ራሳችንን እንመዝንበታለን፡፡

የዘንድሮው በዓል የሚከበረው 2017ን በምናሰናብትበት ዋዜማ ላይ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ “ከትዕግሥት እና ከዕውቀት በተሻለ ሊጣመሩ የሚገባቸው ነገሮች የሉም” ያሉትን የነቢዩን ቃል እናስታውሳለን፡፡

ያለንበት ጊዜ የኢትዮጵያ ማንሠራራት እውን የሆነበት ጊዜ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ፈጣሪ የደከምንበትን ባርኮ የለመንነውን ሰጥቶናል፡፡ የኢትዮጵያ ብልጽግና የበለጠ እውን እንዲሆን ደግሞ ነቢዩ እንዳሉት ዕውቀትና ትዕግሥትን አጣምረን እንጓዛለን፡፡

ዕውቀት ብርሃን ሆኖ ይመራል፡፡ ትዕግሥት ደግሞ ፈተናዎችን በጽናት እንድንሻገር ያደርጋል፡፡ ይሄንንም ከነቢዩ መሐመድ(ሰዐወ) ተምረናል፡፡

“ዛፍ እየተከልክ የፍርድ ቀን ቢደርስ፣ ሳታቋርጥ ዛፍ መትከልህን ቀጥል” እንዳሉት፣ ፈተናዎች ቢበዙም፣ መሰናክሎች ቢደረደሩም እስከ ሕቅታ ድረስ ለሀገራችን እና ለሕዝባችን መልካም መሥራትን እንቀጥላለን፡፡ ከመልካም ሥራ የተሻለ በምድርና በሰማይ ሰውን የሚያስከብር ሕዝን የሚጠቅም ነገር ስለሌለ፡፡

ይሄንን የመውሊድ በዓል የሚያከብሩ ሙስሊም ወገኖቼ ሁሉ፣ መጪውን ዓመት በአላህ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ በሆነው መልካም ሥራ እንዴት እንደምናሳልፈው በመዘጋጀት እንደሚያከብሩት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 2018 የኢትዮጵያን ማንሠራራት በሁሉም ዘርፎች ይበልጥ የምናጸናበት ዓመት በመሆኑ፡፡

መልካም የመውሊድ በዓል ይሁን፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.