የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመረው ሁሉን አቀፍ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)።
መንግስት የጠላትን አደናቃፊ ሴራ ወደ ጎን በመተው የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀመረው ሁሉን አቀፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።
በክልሉ ማረቆ ልዩ ወረዳ በቆሼ ከተማ ለሚገነባው የገራድ ቢመዶ አጠቃላይ ሆስፒታል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ መርሐ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በልማትና በሰላም እሴት ግንባታ ላይ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት በአካባቢው የተለየ ልማት የሚታሰብ አልነበረም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አሁን ላይ ህዝብን በማስተባበር ለልማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የማረቆ ህዝብ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶችና ሴቶች የላቀ ተሳትፎ እንደነበራቸውም አስታውሰዋል።
ከ500 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው የገራድ ቢመዶ አጠቃላይ ሆስፒታል ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የጋራ ትብብርና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ለሆስፒታሉ ግንባታ የሞባይል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ይፋ የተደረገ ሲሆን፥ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በጥላሁን ይልማ