የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እመርታ በወታደራዊ አቅም ማጠናከርና መደገፍ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አጥፍተው የሚጠፉ ድሮኖችን በስፋት እያመረትን እንገኛለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኤሮ ዓባይ የድሮን ማምረቻን የሥራ እንቅስቃሴ በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ አንድን ሀገር ከሚያቆሟት ምሰሶዎች መካከል አንደኛው የኢኮኖሚ ለውጥ ነው ፡፡
አሁን በተጀመረው ሪፎርም የወጪ ንግድም ሆነ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው ፤ ከተሞች እየዘመኑና ፕሮጀክቶችም በጥራትና በፍጥነት እየተጠናቀቁ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እመርታ ከሚያሳዩ በጣት ከሚቆጠሩ ሀገራት ተርታ አንዷ እንደሆነችም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ለሀገር ብልጽግና የሚያስቡ ሰዎች ስብስብ በቀጣይ ሊያስቡት የሚገባው ጉዳይም ወታደራዊ አቅምን ማጠናከር መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በኢኮኖሚ እድገትና ወታደራዊ አቅም በቅደም ተከተል አብረው ማደግ ካልቻሉ ኢኮኖሚው በአቅም ማነስ ምክንያት ተመልሶ ሊበላ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብልጽግና የማያጠራጥር ሐቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በኢኮኖሚ የተጀመሩ ሥራዎችን በወታደራዊ አቅም ማጠናከርና መደገፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለመበልጸግ የሚያስችል ከፍተኛ አቅም እንዳለት ጠቅሰው÷ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና ሌሎች ዘርፎች አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡
ይህ ሁለንተናዊ እድገትም በወታደራዊ አቅም መጠናከር አለበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡
አሁን ላይ አጥፍተው የሚጠፉ ድሮኖችን በስፋት እያመረትን እንገኛለን ፤ እነዚህም የጠላትን ስብስብ ለማጥፋት ከፍተና ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ