Fana: At a Speed of Life!

ምክክር ኮሚሽኑ በካናዳ አጀንዳ ለማሰባሰብ ያዘጋጀው መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብ ያዘጋጀው መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ታሪክ የማይዘነጋቸው ድሎች ብናስመዘግብም ከበርካታ አስርት ዓመታት ወዲህ የማንግባባና ግጭት የማያጣን ሆነናል ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ካላት አኩሪ ታሪክ አንፃር ወደ ፊት መራመድ እንዳልቻለች ገልጸው፤ አለመግባባታችን በመስፋቱ ሀገር የመቀጠላችንን ጉዳይ አጠራጣሪ አድርጎታል ነው ያሉት።

አለመግባባቶቹን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ሙከራዎቹ በኃይል አማራጮች ላይ የተወሰኑ ስለነበሩ ከኪሳራ የዘለለ ፋይዳ እንዳልነበራቸው ገልጸዋል።

የኃይል አማራጮች ሁሉንም አሸናፊ ማድረግ የማይችሉ ስለሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ሳይገኝ እዚህ ደርሰናል ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የምክክር መንገድ ተጀምሯል ብለዋል።

ይህንን ለማሳካት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ ያለመግባባት መንስኤ የሆኑ መሰረታዊ ጉዳዮችን በህዝባዊ ውይይት በመለየት ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሂደቱ ህብረተሰቡ በሀገሩ ጉዳይ ላይ እንዲወስን በማስቻሉ በርካታ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ጠቁመው፤ ዳያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ የሚወስንበት እድል እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በካናዳ እየተካሄደ ያለው መድረክም የዚህ ጥረት አካል መሆኑን ማስረዳታቸውን የምክክር ኮሚሽኑ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ አመላክቷል።
የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) በካናዳ በተጀመረው መድረክ ተሳታፊዎች አጀንዳ ስለሚለዩበትና ስለሚያደራጁበት ስነ ዘዴ ገለፃ አድርገዋል።

አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ እንዲመክሩ መደረጉን ገልጸው፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ እንዲሳተፉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.