Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ የአብሮነት እሴታችንን አጥብቀን መያዝ አለብን – አቶ አወል አርባ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ተጽዕኖዎችን በመቋቋም ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ የአብሮነት እሴታችንን አጥብቀን መያዝ አለብን አሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ “ብዝኃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ የሚገኘውን የኅብር ቀን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዕለቱ የኢትዮጵያውያንን ጥልቅ ትስስር፣ የጋራ እሴትና የብዝኃነት ሀብት በሚገባ ያንጸባርቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ልዩነቷ ውበት፤ አንድነቷ ደግሞ የማይናወጥ ጉልበት ጥንካሬዋ መሆኑን በማውሳት በቋንቋ፣ በባህል፣ በብሔር፣ በእምነትና በሥልጣኔ የበለጸገች ኅብራዊት ሀገር መሆኗን አንስተዋል።

የሀገራችንን ቀለማማ ማንነትና እሴቶች ለማስታወስና ምን ያህል እንደተዛመድንና እንደተወራረስን ለማስተማር ይህ ቀን ታላቅ ትርጉም አለው ነው ያሉት።

የሀገራችንን ነጻነትና ክብር ለማስጠበቅ መስዋዕትነት የከፈሉ አባቶቻችን ለአብሮነት ትልቅ ዋጋ መስጠታቸውን አስታውሰው፥ ከብዝኃነት ባሻገር አብሮነት የህልውናችን ዋስትና እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በደም፣ በኢኮኖሚ፣ በታሪክ እና በባህል የተሳሰረ ታላቅ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህ አብሮነት ሀገራችንን ከማንኛውም አይነት አደጋ በመጠበቅና ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅማችንን በማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የአፋር ሕዝብ እንደ ሌሎች ወንድምና እህት ሕዝቦች የቀደምት ታሪክ ባለቤት፣ ሰላም ወዳድና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የማይደራደር መሆኑን አውስተዋል።

አፋር የእምቅ ሀብት ባለቤትና የኢትዮጵያ የንግድ ኮሪደር መሆኗን ጠቅሰው፥ የአፋር ሕዝብ ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ማንነቱም የኢትዮጵያ ማንነት መገለጫ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የብልጽግናና የከፍታ ሕልም እውን ለማድረግ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ የኮሪደር ልማትና የተፈጥሮ ጋዝ ያሉ ፕሮጀክቶች ወሳኝ መሠረቶችን እየጣሉ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.