Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሰባት አመታት በኢትዮጵያ የተገኙ ኢኮኖሚያዊ እመርታዎች

1. አጠቃላይ ሀገሪቱ ከነበረችበት ውስብስብ የኢኮኖሚና የፋይናንስ አስተዳደር ስርአት ችግር ለማውጣት ባለፉት 7 አመታት የታክስ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ጨምሮ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተደረጉ የለውጥ ተግባራትና ያስገኙት እመርታዊ ውጤት ምንድነው?

• የኢኮኖሚ ዕድገት፡ ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ካሉበት ተግዳሮቶች እየተላቀቀ እንዲሄድ አስችለዋል፡፡ በዚህ ረገድ ተዳክሞ የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት አንሰራርቷል፤ ኢኮኖሚው ከ2010-2016 ባሉት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ የ7.2 በመቶ እያደገ የነበረ ሲሆን፣ በ2017 በጀት ዓመት ከ8.4 በመቶ ዕድገት በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

• ኤክስፖርት አፈጻጸም፡ ከ2010-2016 ባሉት ዓመታት 3.4 ቢሊዮን አሜሪካን ዶላር በአማካይ በየዓመቱ ከኤክስፖርት ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ የዛሬ ዓመት ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በታሪክ ከፍተኛ የሆነውን የ8.3 ቢሊዮን አሜሪካን ዶላር ገቢ ከኤክስፖርት ሊገኝ ችሏል።

• የመንግስት ገቢ፡ የመንግስትን ገቢ አፈጻጸም አሁን ካለበት ዝቅተኛ ደረጃ ለማሻሻል በርካታ የታክስ ፖሊሲና የታክስ አስተዳደር ማሻሻያዎች ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ ለአብነትም፣ የኤክሳይዝ ታክስ እና የተ.ዕ.ታ አዋጅ ማሻሻል፤ አዲስ የማህበራዊ ልማት ታክስ ይጠቀሳሉ። በነዚህና ሌሎች የታክስ ማሻሻያ ምክንያቶች የፌዴራል መንግስት ከታክስ ምንጭ የሚሰበስበው ገቢ በ2017 በጀት ዓመት ከ80 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ይህም የታክስ ገቢ ላለፉት ዓመታት ሲያሽቆለቁል የነበረውን የታክስ ገቢ ለአጠቃላይ ሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ድርሻ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ከወዲሁ ያመላከተ ነው [መጠኑ በቀጣይ የብሔራዊ አካውንት መረጃ ይፋ ሲሆን የሚታወቅ ይሆናል]።

• የዋጋ ንረት፡ መንግስት በወሰዳቸው ዘርፈ-ብዙ ርምጃዎች ምክንያት ለተከታታይ ዓመታት የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረትም በአንጻራዊነት እየቀነሰ መጥቷል።

2. የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በፊስካልና በገንዘብ ፖሊሲ ላይ የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ እመርታዎች

• የተረጋጋ ዋጋን ዕድገትን ለማስፈን የተለያዩ የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃዎች ተግባራዊ ተደርገዋል። ከነዚህም መካከል፦

o የብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር፡ የመንግስትን የበጀት ጉድለት ለመሸፈን ከብሔራዊ ባንክ የሚወሰደው የቀጥታ ብድር ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር ተደርጓል፤

o መሰረታዊ ሸቀጦች ድጎማ፡ የነዳጅ፣ የማዳበሪያ፣ የመድሃኒት፣ ለዘይት ድጎማ ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፤

o የብድር ጣሪያ ፖሊሲ፦ የንግድ ባንኮችን የገንዘብ መስፋፋት (money creation) ለመገደብ የሚያስችል የብድር ጣሪያ (ቀደም ስል 14% በኋላም ወደ 18% ከፍ እንዲል ተደርጓል)፤

o የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔን (15%) በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ አድርጓል፤

o ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተለያዩ ጊዜያት ገንዘብ የመሰብሰብ የጨረታ ገበያዎችን (liquidity absorbing open market operations) በመካሄድ የገንዘብ ዕድገት በመቆጣጠር ዋጋ የማረጋጋት ስራዎች ተሰርቷል። በተጨማሪም የተቀማጭ ገንዘብ (reserve money) እና የገንዘብ አቅርቦት (broad money) ዕድገታቸው ተገድቧ፤

o ምርትና ምርታማነት ማሳደግ፡ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት በተሰሩ ስራዎች አቅርቦትን በማሳደግ ከፍተኛ የዋጋ ንረትን በዘለቂነት ለመፍታት ተሞክሯል።

o የአቅርቦት ሰንሰለት ውጤታማነት ማሻሻል፡ ሰው ሰራሽ እጥረቶችን በመፍጠር የሚስተዋለውን የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የተለያዩ ተግባራት ተከናውኗል።

• በነዚህ ምክንያቶች ለተከታታይ ዓመታት የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረት በአንጻራዊነት እየቀነሰ መጥቷል። አጠቃላይ ሀገራዊ የሸቀጦች ዋጋ ዕድገት በነሐሴ 2014 ላይ 34.5 በመቶ ከፍተኛ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ መንግስት በተከታታይ በወሰዳቸው በተጣጣመ የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲ ርምጃዎች የተነሳ በሰኔ 2017 ወደ 13.9 በመቶ ዝቅ ብሏል።

3. በውጭ ምንዛሬ ላይ በተደረገው ማሻሻያ በኢንቨስትመንት በወጭ ንግድ እንቅስቃሴ አጠቃላይ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች

• የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያዎች እና ጥብቅ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲዎች ተግባራዊ በመደረጋቸው ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የተገኙት ዋና ዋና ውጤቶች፣

o በህጋዊና በተጓዳኝ ገበያው መካከል ያለው የውጭ ምንዛሬ ምጣኔ ልዩነት (premium) በከፍተኛ ደረጃ መጥበብ ችሏል፡፡ በዚህም በሐምሌ 2016 መጨረሻ የነበረው የ96% ልዩነት ሰኔ 2017 መጨረሻ ላይ ወደ 14.4 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡

o በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከእጥፍ በላይ በማደግ 8.3 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 3.8 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር የ119 በመቶ ብልጫ ያለው ነው። በአንጻሩ ለኢምፖርት የሚከፈው መጠን እምብዛም ባለመጨመሩ የንግድ ሚዛን ጉድለት ከሌላው ጊዜ አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ ጠቧል።

o የውጭ ምንዛሬ በገበያ ሥርዓት እንዲወሰን ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በሀዋላ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ በባንኮች በኩል የተላከ ገንዘብ መጠን ጨምሯል፡፡

o የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

o መንግስት ከውጭ ንግድ የሚሰበስበው የታክስ ገቢ ጨምሯል።

4. የብድር አስተዳደርና የመንግስት ዕዳ፡ የመንግስት እዳ ሽግሽግ እና የተሻለ የብድር አስተዳደር

• የመንግስት ብድር (public debt) ጤናማ እንዲሆን በዕዳ ሽግሽግና ቅነሳ ከአበዳሪዎች ጋር ውጤታማ ድርድሮችን በማካሄድ የሀገሪቱን የዕዳ ስጋት ደረጃን ወደ መካከለኛ ስጋት ደረጃ ለማውረድ እየተሰራ ይገኛል።

• ኢትዮጵያ ከኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ (OCC) ጋር የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረመች በኋላ ከ3.5 ቢሊየን ዶላር የእዳ ሽግሽግ ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡

5. የኢኮኖሚው እድገትና የለውጥ ተግባራት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን ታሳቢ በማድረግ በኩል አተገባበሩ ምን ይመስል ነበር

• በመጀመሪያ ደረጃ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎች ተግባራዊ በሚደረጉበት ወቅት በተቻለ መጠን ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ጉልህ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። ለአብነትም የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ለውጥን ተከትሎ ሊከሰት በሚችለው የዋጋ ንረት ምክንያት ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኙ የህብረሰብ ክፍሎች እንዳይጎዱ የተለያዩ ድጎማዎች (በነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ የምግብ ዘይት) እንዲሁም ልማታዊ ሴፍቲኔት ተደራሽነትን በማስፋት እና ዝቅተኛ ደመወዝ ለሚያገኙ የመንግስት ሰራተኞቸ የደመወዝ ማስተካከያ መደረጉ ይታወሳል። በተመሳሳይ ሌሎች የፖሊሲ ማስተካከያዎች በሚደረጉበት ወቅት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ከፍሎችን ከግምት እንዲያስገባ ተደርጓል (ለምሳሌ፦ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ progressive እንዲሆን፣ በተ.ዕ.ታ ማሻሻያ ደግሞ ደሃው ህብረተሰብ በዋናነት የሚጠቀማቸውን ምርቶች ነጻ አድርጎታል)።

• በሌላ በኩል የእነዚህ ሁሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ዋናኛው ግቡ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ ልማትን ማረጋገጥ ነው። በመጨረሻም ሰፋፊ የስራ እድሎችን በመፍጠር እና ዝቅተኛ የዋጋ ንረትን በማስፈን ብሎም የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችል ይሆናል። እነዚህ ነገሮች በቅደም ተከተል የሚሆኑ ከመሆኑ ባሻገር የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ተግባራዊ ከተደረጉ በኋላ በሂደት የሚሳኩ ግቦች ናቸው።

#የገንዘብ ሚኒስቴር

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.